የቀድሞው ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ሥር የተደራጁ ተቋማት አመራሮች
የተቋም ትውውቅ አድርገዋል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ሙፈሪያት ካሚል ለተቋሙ
የተሰጠው ኃላፊነት ትልቅ መሆኑን አስታውሰው የነበረውን አሠራር መረዳት አገርን የማሻገርን ተግባር በስኬት ለመወጣት
የመጀመሪያው ምዕራፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ተቋማቶቹ በነበራቸው መልካም ተግባር የተጨመሩትን አዳዲስ ሥራዎች
በማካተት አገራዊ ተልዕኮውን በጋራ ለማሳካት እንሠራለን ብለዋል፡፡
የሥራ ፈጠራ አጀንዳ ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ጉዞ ወሳኝ እና የብዙ ችግሮቻችን መፍትሔ መሆኑን በማመን በአዲሱ
የመንግስት አወቃቀር ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የሆነው ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር
ተቋቁሞ የሥራ እና ሠራተኛ ተግባራትን እያከናወኑ የሚገኙ ተቋማት በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ስር እንዲሆኑ መደረጉን
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ የሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መቋቋም ቀደም ሲል ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ሲያከናውን የነበረውን ለዜጎች
የሥራ ዕድል ለማመቻቸት የማስተባበር እና የማቀናጀት ተግባር ከፍ ያደርገዋል ብለዋል።
በዚህም መሰረት ለሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጡ አሠሪና ሠራተኛን የሚመለከቱ ሥልጣንና ተግባራት፣
ለሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ተሰጥተው የነበሩ ስልጣንና ተግባራት፣ ለፌዴራል ከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ
ዋስትና ኤጀንሲ ሥራ ፈጠራን የሚመለከቱ ሥልጣንና ተግባራት፣ ለግብርና ሚኒስቴር የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ
ተሰጥተው የነበሩ ሥልጣንና ተግባራት ለተቋቋመው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የተሰጡ ሲሆን የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና
ኢንስቲትዩት፣ የግብርና ቴክኒክና ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጆች፣ የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ለሚኒስቴር መሥሪያ
ቤቱ ተጠሪ ተቋማት መሆናቸው ተጠቁሟል ።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ሦስት ሚኒስትር ዴኤታዎች እና አንድ አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ተሾሞለታል፤ በዚህም
መሰረት አቶ ንጉሡ ጥላሁን የሥራ፣ የሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ፣ ዶ/ር በከር ሻሌ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ
ሚኒስትር ዴኤታ፣ አቶ አሰግድ ጌታቸዉ የሠራተኛ ጉዳይ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ፣ ወ/ሮ ነብያ መሀመድ አማካሪ ሚኒስትር
ዴኤታ ሆነዋል፡፡
በትውውቅ መድረኩ በአዲስ መልክ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ስር የሚዋቀሩት እና ተጠሪ የሚሆኑት ተቋማት
የእስካሁኑን ሂደታቸውን ፣ ያመጡትን ውጤት እና ያጋጠሟቸውን ችግሮች በተመለከተ ገለፃ ካደረጉ በኋላ ውይይት
ተደርጎባቸዋል፡፡

ያጋሩት