የኢ.ፌ.ድ.ሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በሁሉም የሥራ ዘርፎች የሥራ ዕድል ፈጠራ አጀንዳን የማስተዳደር ፣ የማቀናጀት እና የመቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው እ.ኤ.አ በ2018 ዓ.ም በሚኒስትሮች ም/ቤት በጸደቀው ደንብ ቁጥር 435/2011 መሰረት ተጠሪነቱ ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኖ የተቋቋመ መንግስታዊ ተቋም ነው። ኮሚሽኑ በመላ አገሪቱ የሚፈጠሩ ሥራዎች ዘለቄታ ያላቸው እንዲሆኑ በ 2012 ዓ.ም- 3ሚሊዮን ፣ እስከ 2017 ዓ.ም – 14ሚሊዮን ፣ እስከ 2022 ደግሞ 20 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ በማመቻቸትና ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ይህንን ሀገራዊ ዓላማ ለማሳካትም በጀት ዓመቱ ሊፈጠሩ ከታቀዱት 3,000,000 የሥራ ዕድሎች ከፍ ባለ አፈጻጸም 3,326169 የተፈጠሩ ሲሆን ከነዚህም 62%(2,062,225) ቋሚ ፣ 38%(1,263,944) ጊዜያዊ ዕድሎች ፤ በጾታ ድርሻ – 35.5% (1,180,790) ሴቶች ፣ 64.5%(2,145,379) ወንዶች ፤በቦታ ድርሻ ደግሞ 48% (1,396,991) በገጠር የሚገኙ ፣ 52% (1,929,178) ደግሞ በከተማ የሚገኙ ናቸው። በ2012 ከተፈጠሩት ጠቅላላ የሥራ ዕድሎች መካከል 330,971 ሥራዎች በኮቪድ 19 ተጽዕኖ ምክንያት ከስመዋል።
ለዚህ ስኬታማ አፈጻጸም አስተዋጽዖ ካደረጉት ነገሮች መካከል ጠንካራ የዝግጅት ምዕራፍ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። በዚህ ወቅትም በኢ.ፌ.ድ.ሪ ጠ/ሚኒስትር የሚመራ የሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደር ፕሬዘዳንቶችና ከንቲባዎች እንዲሁም ወሳኝ ሚና ያላቸው ሚንስትሮች ያሉበት የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንቨስትመንት መሪ ኮሚቴ ፤ በኢ.ፌ.ድ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴር መሪነትና በክቡር ኮሚሽነሩ ጸሃፊነት የሚመራ ሀገር አቀፍ የሥራ ፈጠራ አጀንዳውን የሚያስተባበር እንዲሁም ዕቅድና አፈጻጸምን የሚገመግምና አቅጣጫ የሚያስቀምጥ 41 አባላት ያሉት የሥራ ዕድል ፈጠራ ብሔራዊ ምክር ቤት ፤ በብሔራዊ ሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት የሚወሰኑ ዋና ዋና ውሳኔዎችን የሚያስፈጸም የዋና ዋና ሚንስቴር መስሪያ ቤቶች ኮሚቴ ፤ በየሶስት ወሩ እየተገናኘ የዘርፉን እቅድና አፈፃፀሙን የሚገመግምና የሚመራ የፌደራልና ክልሎች የሥራ ዕድል ፈጠራ አካላት የጋራ መድረክ ተቋቁሞ ሁሉም አካላት የሥራ ዕድል ፈጠራን በአጀንዳነት እንዲይዙት መደረጉ የሚጠቀስ ነው።
የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራውን ለመደገፍ የሚያስፈልግ ሀብትም ከተለያዩ አካላት ለማሠባሠብ የተደረገው ጥረትም ስኬታማ የሚባል ሲሆን በበጀት ዓመቱ ሊሰባሰብ ከታቀደው 500 ሚሊዮን ዶላር ከልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በተደረገው ስምምነት እንደ ሃገር ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚውል 384.9 ሚሊዮን ዶላር (77%) ሃብት ማሰባሰብ ተችሏል።
በተጨማሪም የኮሚሽኑን አጠቃላይ ተልዕኮና ራዕዩን ለልማት አጋሮችን በማስተዋወቅ እና በጋራ ሊሰሩ የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በዓመቱ ከ22 የልማት አጋሮች ጋር አጋርነት ለመፍጠር ታቅዶ ከ 10 ለጋሽ፣ 5 ተራድዖ እና 5 የግሉ ዘርፍ በድምሩ ከ 22 አጋር አካላት ጋር ስምምነት ተፈጽሟል።
ዘርፉ ከዚህ በፊት የሚመራበት ሀገራዊ ስትራቴጂክ የሥራ ዕድል ፈጠራ እቅድ ስላልነበረውና ግልጽና ሊለካ የሚችል ውጤት ስለሚያስፈልገው የአስር ዓመት ፍኖተ ካርታና የአምስት ዓመት (እስከ 2017 ዓ.ም) ዝርዝር ስትራቴጂክ እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ተገብቷል። ይህ እቅድ በርካታ የግሉንና የመንግስትን ዘርፍ ተወካዮችንና ሥራ ፈጣሪዎችን አሳትፎ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ባለሙያዎች አስተዋፅኦ የተዘጋጀ ሲሆን የ25አገራትን ተሞክሮ ያገናዘበ እቅድ ነው።
ሰፋፊ የሥራ ዕድሎችን ለማመቻቸት በሚደረገው ጥረትም ሥራ የመፍጠር አቅም ያላቸው ሆኖም ብዙ ያልተሰራባችውን ሴክተሮች ኮሚሽኑ ከግሉ ሴክተርና ከልማት አጋሮች ጋር በመሆን የሚያስተገብራቸውንና የፈጠራ ሃሳብ የታከለባቸውን ፕሮጀክቶችን ቀርጾ በትግበራ ላይ ይገኛል።
ከነኝህም በዋናነት ተጠቃሽ የሆኑት ፋብሪካ ምርቶችን ከፋበሪካ በየቤቱ ለተጠቃሚዎች የማቅረብ ፕሮጀክት ፣ዲጂታል መተግበሪያዎችን በመጠቀም የገንዘብ ክፍያዎችን የመፈጸም ፕሮጀክት፣ በስልክ ጥሪ የሚደረግ የጠቅላላ የጥገና አገልግሎት ፣ የገጠር የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች ከ3 እስከ 5 ዓመታት የሚዘልቁ ሲሆን ለ128,000 ሰዎች የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራሉ። በተጨማሪም በኮሚሽኑ ድጋፍ የተጀመሩ 5 የረጅም ጊዜ ፕሮ ክቶች ሲኖሩ በአጠቃላይ 1.3ሚሊዮን የሥራ ዕድሎችን በ5 ዓመታት ለመፍጠር የታቀዱ ናቸው።
የውጪ ሀገር የሙያ አገልግሎት አቅርቦት (የሥራ ስምሪት) የሰለጠነና በከፊል የሰለጠነ የሰው ኃይልን በውጪ ሀገር የሥራ ዕድል እንዲያገኝ፣ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን የሥራ ስምሪትና የመርከብ ላይ ሥራ(መርከበኞችንና ተጓዳኝ ሥራዎችን የሚሰሩ ሰራተኞችን በማሰማራት) በርካታ የሥራ እድሎችን የማመቻቸት ትልቅ አቅም ያላቸው በመሆኑ በኮሚሽኑ ተጀምረው የመንግስትንም ትኩረት ስበዋል። ፕሮጀክቶቹ የተለዩት ንድፈ ሃሳቡ በኮሚሽኑ ቀርቦ የተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ባለሙያዎች፣ አማካሪ ድርጅቶቸ፣ የንግድ ሰዎች፣ በአንድ ላይ በመሆን ሃሳቡን ካዳበሩት በኋላ በአማካኝ አንድ ወር ተኩል የፈጀ ጥናት ተካሂዶ የመጀመሪያዎቹ 16,000 የውጭ ሀገር ሥራዎች ተፈጥሯል።
የሥራ ገበያ መረጃ ጥራትን ለማሻሻል ኮሚሽኑ እንደ ሀገር የሥራ ገበያ መረጃ ስርዓትን ለመዘርጋት በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሰረት በ2012 በጀት ዓመት የሚሰበሰበው የሥራ ገበያ መረጃ ጥራት ከፍ እንዲል እና የመረጃ አያያዝ ጥራትን ለመጨመር ሥራ ፈላጊዎችን የሚመዘግብ የሞባይል መተግበሪያ (#etworks) እና የውጭ አገር የሥራ ቅጥር መመልመያና ስምሪት መመዝገቢያ ሶፍትዌር አዘጋጅቷል።
በዓመቱ አፈጻጸም ካጋጠሙ ማነቆዎች መካከል ዋነኛውና በአሁኑ ሰአት የአለማችን ብሎም የሀገራችን ትልቅ ተግዳሮት የሆነው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አንዱ ነው። ለዚህም ኮሚሽኑ ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራና እና የነፍስ ወከፍ ገቢ ላይ ሊያስከትል የሚችላቸው ተግዳሮቶች ታሳቢ ያደረገ የአጭር ጊዜ ምላሽና የረጅም ጊዜ የመልሶ ማገገሚያ (Recovery) እቅድ አዘጋጅቷል። በእቅዱ መነሻነትም በወረርሽኙ ለተጎዱ ኢንተርፕራይዞች ማገገሚያ የረዥም ጊዜ የብድር ዋስትና የሚሆን 28 ሚሊዮን ዶላር ሃብት ከለጋሽ ድርጅቶች ማሰባሰብ ተችሏል። በተጨማሪም የሥራ ፈጣሪዎችን ጥረት በመደገፍ በኮቪድ-19 ተጽዕኖ ውስጥ ለወደቁ 11 ኢንተርፕራይዞች ድጋፍ በማድረግና በቅርቡም የባንክ ብድር ዋስትና ለመስጠት ውድድርን መሰረት ያደረገ የድጋፍ ፕሮግራም ለመጀመር ዝግጅት ተጠናቅቋል።
ወረርሽኙ አሁን ባለበት ደረጃ ሳይስፋፋ በፊትም በሥራ ዕድል ፈጠራ እንቅስቃሴውና በአገሪቱም ኢኮኖሚ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ጫና በመገመት አማራጭ የፖሊሲ ምክረ ኃሳቦችን የሚዳስስ ጥናትና ትንተና በመሥራት ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አስተላልፏል። በጥናቱ መነሻነትም ለማህበረሰቡ የማነቃቂያ ዌቢናሮችንና አስፈላጊ መረጃዎችን ሲያስተላልፍ ቆይቷል። የበጀት ዓመቱ አፈጻጸም ከታቀደው አንጻር የተሻለ ቢሆንም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እስካሁን ባስከተለውና ወደፊትም ሊያስከትል በሚችለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ምክንያት በርካታ ሥራዎች ስጋት ውስጥ ሊወድቁና በርካታ ኢንተርፕራይዞችም ገቢያቸው እንደሚቀንስ በማወቅ ከፍተኛ የሆነ ርብርብ ይጠይቃል።
በኮቪድ-19 ተጽዕኖ ምክንያት የሚፈጠረውን ጫና ለመቋቋምና ከ2012 በተሻለ በበለጠ አፈጻጸም ለማከናወን ተጨማሪ የሃብት ማሰባሰብ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን በተለይም የልዩ ፕሮጀክቶች ትግበራ፣ የአገልግሎት ኤክስፖርትና የወጣቶች የሥራ ባህልና የክህሎት ግንባታ ሥራዎች እንዲሁም ሥራፈጣሪዎችን ወደ ኢንተርፕራይዝነት የማሳደግ ሥራዎች ላይ ካለፈው ዓመት ከተገኙ ልምዶችና ተጨባጭ የአገሪቱ ፍላጎቶች ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ እንዲሁም ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ በጎዳና የሚኖሩ ወጣቶችንና ሌሎች ልዩ ልዩ ትኩረት ያልተሰጣቸው የማህበሰብ አካላትን በሚያካትት መልኩ በመጪው የበጀት ዓመት ተጨማሪ 3 ሚሊዮን የሥራ ዕድሎችን ለማመቻቸት ኮሚሽኑ ከሌሎች ባለድርሻ አካላትና የግሉ ዘርፍ ጋር በከፍተኛ ቅንጅት በሙሉ አቅሙ በቆራጥነት ይሰራል።
ለዚህ ዓመት ስኬታማ አፈጻጸም ከፍተኛ የአመራርና የፈጻሚነት ሚናቸውን ለተወጡ የፌደራልና የክልል የሥራ ዕድል ፈጠራ አካላት እንዲሁም የዘርፍ ከፍተኛ አመራሮችን ኮሚሽኑ ከልብ ለማመስገን ይወዳል።
ያጋሩት