በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በተደረገ አገር አቀፍ ጥሪ ሲደረግ የነበረው ውድድር እና ስልጠና ተጠናቆ ከተመዘገቡት
462 ሃሳቦች 30ዎቹ ለሽልማት በቅተዋል፡፡ ለሥራ ፈጠራ ሃሳብ አመንጪዎቹ ሽልማት ያበረከቱት የሥራ እና ክህሎት
ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ሙፈሪሃት ካሚል የተመለከትናቸውን የፈጠራ ሃሳብና ውጤቶችን አግዞ ወደተግባር
መቀየር ከተቻለ እንደ አገር ብሩህ የሆነ ጊዜ እንደሚጠብቀን ያሳያል ብለዋል፡፡
ወጣቶቹ ቁጥራቸው ትንሽ ቢመስልም ኢትዮጵያ ያልተነኩ እምቅ አቅሞች እንዳሏት ማሳያ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በወጣቶቹ የተፈጠሩት የሥራ ሃሳቦች የሥራ ዕድል ለራሳቸውም ለሌሎችም ለመፍጠር ትልቅ ጉልበት ያላቸው መሆኑን
መስክረው ወጣቶቹም የሚገጥሟቸውን ተግዳሮቶች ተቋቁመው ለሌሎችም ተስፋ እንዲሆኑ አሳስበዋል ክብርት
ሚኒስትር ሙፈሪሃት፡፡
የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ስለ
ብሩህ የሥራ ፈጠራ ሃሳቦች ሁለተኛው ዙር ውድድር ሲያብራሩ በተለያዩ ሚዲያዎች የቀረበውን ጥሪ መሠረት በማድረግ
በመጀመሪያ ከተመዘገቡት 462 የሥራ ፈጠራ ሃሳቦች በተለያዩ ዙሮች ተመዝነው ለሽልማት የበቁት የ30 የንግድ
ፈጠራ ሃሳቦች ባለቤት የሆኑ ወጣቶች ሃሳባቸው ለዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ፣ ወደ ተግባር የሚቀየር እና ችግር
የሚፈታ መሆኑ ከተመረጡበት መስፈርት መካከል ይጠቀሳል ብለዋል፡፡ወጣቶቹ የንግድ ሥርዓትን እና ክህሎትን
የተመለከቱ ስልጠናዎች ተሰጥቷቸው ለሽልማት እንደበቁም አብራርተዋል፡፡
ብሩህ የንግድ የፈጠራ ሃሳብ ውድድር ከተባበሩት መንግሰታት የልማት ፕሮግራም እና ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር
በትብብር የሚካሄድ ሲሆን ተሸላሚዎች ለንግድ ፈጠራ ሃሳባቸው 5ሺ ዶላር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በብሩህ የንግድ የፈጠራ ሃሳብ ውድድር ሽልማት በመጀመሪያው ዙር 17 የንግድ ፈጠራ ሃሳቦች ለሽልማት መብቃታቸው
ይታወሳል፡፡

ያጋሩት