“ህልምን እውን ለማድረግ እያንዳንዱን ርቀት መጓዝ- Walk every mile to make yourdream come true!”

የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራ እንደዛሬው በስፋት ባልተለመደበት ጊዜ ከስምንት ዓመታት በፊት ሃና ዮሐንስ ሥራውን በድፍረት ጀመረች፡፡

ዘርፉ በሥራ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም እራሱን ችሎ እንደትምህርት የማይሰጥ እንደነበር ሃና ትናገራለች ፡፡

እሷ ምንነቱን ለይታ አውቃ እንድትማረውና ወደ ዘርፉም እንድታዘነብል ያደረጋት በአንድ ወቅት በቴሌቭዥን መስኮት ያየችው ፕሮግራም እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

ድሮ ድሮ ፋሽን ላይ ነበር ፍላጎቴ፡፡ እንደውም የመጀመሪያ ልብስ ስፌት ማሽኔ የተገዛልኝ በ13 ዓመቴ ነበር፡፡

ከዛ በኋላ ግን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ የኦፕራ ዊንፍሪ ሾው ይታይ ነበር፤ እና እዛ ላይ ኔት በርክስ የተባለ የኢንቴሪየር ዲዛይን ፕሮግራም ስታቀርብ አየሁ፡፡ ከዛ እኛ ሀገር ጭራሽ ያልተነካ ሥራ እንደሆነ ፣ ሀገርኛ ይዘት ብንጨምርበት የበለጠ እንደሚያሰራ ተረዳሁ፤ ፍላጎትም አደረብኝ፡፡ ወዲያው ስለ ኢንቴሪየር ዲዛይን የበለጠ ማንበብ እና ጥናት ማድረግ /ሪሰርች መሥራት/ ጀመርኩኝ” ትላለች ሃና፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንደጨረስኩ ግን በኢትዮጵያ ለኢንቴሪየር ዲዛይን የሚቀርብ ትምህርት ያገኘሁት የህንፃ ዲዛይን(አርክቴክቸር) ስለነበር ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ገብቼ ተማኩ፡፡

ጎን ለጎን የውጭ ሀገር ትምህርት እሞክር ስለነበር ፍላጎቴን ለማሳካት ድል ቀንቶኝ ለንደን ወደሚገኘው አሜሪካን ኢንተር ኮንቲነንታል ዩኒቨርሲቲ አቀናሁ፡፡ በ2005 .ም ትምህርቴን ጨርሽ እንደመጣሁ ምንም አይነት የመቀጠር ፍላጎት አልነበረኝም፡፡”

ሥራ ፈጣሪ መሆን የፈለገችው ሃና አንድ ብላ ስትነሳም የኢንቴሪየር ዲዛይን አማካሪ ቢሮ ከፍታ እንደነበር ታስታውሳለች ፡፡

ንግድ ፍቃድ ስለማውጣትም ሆነ ቢሮ ስለመክፈት ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡ 6 ወር ነበር የፈጀብኝ! ፀሀይ ለፀሀይ የተንከራተትኩበት ፊቴ ራሱ ማዲያት አውጥቶ ነበር፡፡ ቢሮው ተከፍቶም ግን ሥራው እንደጠበኩት አልጋ በአልጋ አልሆነልኝም ነበር፡፡

ከታክስ አከፋፈል ጀምሮ ደምበኛ እንዴት እንደሚገኝም ሆነ በዘርፉ ቢዝነስ እንዴት እንደሚሰራ ምንም አልገባኝም ነበር፡፡ ከዛ በኃላ የሆነ ጊዜ የካክተስ ኮሚውኒኬሽን ኃላፊ ሥራ ሊያሰራኝ መጣ ነገር ግን ልምድ እንዳልነበረኝ ወዲያው ስለገባው ለቢዝነሱ አዲስ ብሆንም የዲዛይን ብቃቱ እንዳለኝ ነገርኩት ፡፡ እሱም ቢዝነሱ እንዴት እንደሚሰራ ሊያስተምረኝ ፍቃደኛ ስለነበር ቢሮውን ዘግቼ እሱ ጋር እንድቀጠር አማራጭ አቀረበልኝ፤ ሳላንገራግር ተቀጠርኩ፡፡

ምንም እንኳን ካክተስ የኮሚውኒኬሽን እና የማስታወቂያ ሥራ መስሪያ ቤት ቢሆንም የራሴን ክንፍ እንደፈጠረልኝና ለቀረፃ የሚሆኑ ቦታዎችን በመገንባት ኢንቴሪየር ዲዛይንን በደምብ እንድለማመድ ዕድል ከፈተልኝ ፡፡

ደሞዜ በጣም ትንሽ ነበር ፡፡ ነገር ግን ያፈራሁት ግንኙነቶች እና የቀሰምኩት ልምድ እጅግ ብዙ ነው፡፡ እዛ ድርጅት ለሚሰሩ ቪዲዮች አልባሳት እና የቀረፃ ቦታን ከመገንባት ባለፈ ከአለቃዬ ጋር በጥምረት ቦሌ አለም ህንፃ ጀርባ የሚገኘውን ዘመን ባንክን ሰርቼ ነበር፡፡ በጊዜው ለእኔ ከባድ እና ትልቅ ነገር ነበር፡፡

5 አመታት ያህል በካክተስ ተቀጥሬ ከሰራሁ በኋላም ያሁኑን ድርጅቴን ‘ዘ ሉክ ኢንቴሪየር’ ኃ.የተ.የግ.ማን በ2009 .ም መሰረኩ፡፡ የተጀመረውም በ40ሺህ ብር መነሻ ካፒታል እና በጠባብ ቢሮ ነበር፡፡

በቅጥር ላይ እያለሁ በመጨረሻ የተከፈለኝ ክፍያ ላይ ቤተሰቦቼ ቀስ ብዬ የምከፍለው ገንዘብ ጨመሩልኝ፡፡

ከዛ 2 ማሽኖች ገዝቼ ቢሮዬ ጠባብ ስለነበር ቤተሰቦቼ ቤት ውስጥ ነበር ዋናውን ሥራ የማሰራው፡፡

በተጨማሪም ካክተስ እያለሁ ከጥሬ እቃ አቅራቢዎች እስከ ደምበኞች ድረስ ጥሩ ግንኙነቶችን አፍርቼ ስለነበር፣ የካክተስ አለቃየዬም ሥራዎች ሲመጡ ወደ እኔ ስለሚልክ አሁን እንደመጀመርያው አልከበደኝም፡፡

ድርጅቴ ያላለቁ የንግድ እና የመኖሪያ ፎቆችን ፣ ካፌዎችን፣ ባንኮችን እና የመሳሰሉትን ውስጣዊ ገፅታ መገንባት እና ቁሳቁሶችን ማሟላት ሥራን የሚሰራ ሲሆን ጎን ለጎን ደግሞ በሽመና ሥራ የታገዙ የሶፋ ትራስ እና መጋረጃ ጨርቆችን እንዲሁም ሌሎች የቤት ውስጥ ማስዋቢያ ቁሶችን ይሰራል፡፡

በሥራላይ ታዲያ ገበያ የማግኘት ችግር እምብዛም ባይገጥመኝም ሴት በመሆኔ ብቻ እምነት ማግኘት ከባድ ሆኖብኝ ነበር፡፡

መጀመያ ስለሥራው ስነጋገር ሴት ስለሆንኩኝ ‘ትሰራዋለች ወይ’ የሚል ጥርጣሬ እና ያለማመን ነገር ሁሌም ፊታቸው ላይ በግልፅ አያለሁ፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ ሴት ሲኮን በመናገር ሳይሆን በመስራት ነው መታመን፣ ብቃትን ማሳየት የሚቻለው፡፡ እኔም ይሄ ነገር ሁሌ ያጋጥመኛል፡፡

አንድ የማስታውሰው ቀላል ገጠመኝ አለ እንደውም የምሰራውን ነገር እየለካሁ ሥራውን የምሰራለትን ሰው ፍላጎቱን እና የቀለም ምርጫውን ስጠይቀው እየደጋገመ መልስ ሲሰጥ የነበረው አብሮኝ ለመጣው ወንድ የሥራ ባልደረባዬ ነበር፡፡ ሥራውን የምሰራው እና የማዋራው እኔ እያለሁ ሰውየው የሚመልሰው ግን ለወንዱ ነበር፡፡ በዚህን ያህል መጠን ከቁም ነገር አለመወሰድ እንግዲህ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ማሰብ ይቻላል፡፡”

እንደዚህ አይነት ነገሮች ሲያጋጥሙ መፍትሄው በትዕግስት በማለፍ ሥራውን በብቃት ሰርቶ ማሳየት እንደሆነ ሃና ትናገራለች ፡፡

አሁን ካሉኝ 24 ሠራተኞች 16ቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ፍላጎቴ ሴት ወደመቅጠር ያደላል፡፡ የግንባታው ዘርፍ ላይ በብዛት የሚታዩት ወንዶች ናቸው፤ ያንን ለሴቶች ዕድል በመስጠት ማስተካከል እፈልጋለሁ፡፡

ከአስቸጋሪ አጋጣሚዎቼ የቅርቡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለእኔም ሆነ ለሠራተኞቼ ትልቅ ዱብዳ ሆኖብን ነበር፡፡

በጣም ነበር የደነገጥኩት ፤ሠራተኛ ለመቀነስ ማሰብ ጀምሬ ነበር፡፡ ምክንያቱም ሥራችን ሙሉ ለሙሉ ነበር የቆመው፡፡ ሥራ ከሌለ ደግሞ የሠራተኛ ደሞዝ በምን ይከፈላል? ከዛ ምንም ባልጠበኩት ሁኔታ በሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በኩል የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ መጣልን፡፡

ድጋፉ በብር ቢተመን ወደ 160ሺህ ብር ገደማ ነው ፡፡ ያዋልነውም ለማሽኖች ግዢ፣ ተጨማሪ የሠራተኞች ቅጥር እና ለጠቅላላ ሠራተኞቻችን እስከ 4 ወር ድረስ የደሞዝ ክፍያ እንዲሁም የጥሬ እቃ ግዥ ላይ ነው፡፡

ማስተርካርድ ባይኖር እንዴት ልንሆን እንደምንችል ማሰብ ይከብደኛል፡፡ እኛ የምናገኛቸውን ገቢ እና ትርፎች ማን እና ጥሬ እቃ ነበር የምንገዛበት ይሄ አጋጣሚ ግን ለግል ብቻ ሳይሆን እንደ ድርጅት እንዲህ አይነት ከባድ ፈተናዎች ሲገጥሙ መቋቋም የሚያስችል ቁጠባ ሊኖረን እንደሚገባ ነው ያስተማረኝ፡፡

እግዚያብሄር ይመስገን የተደረገልን ድጋፍ በእግራችን እንድንቆም ብቻ ሳይሆን በማሽንም በቁጥርም እንድናድግ ነው ያደረገን፡፡ አሁን 45 ሠራተኞች አሉኝ፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ስለመቀነስ ማሰብ አልፈልግም፡፡ እንዲያውም መጨመር ነው የምፈልገው፡፡

200ሺህ ብር ካፒታል የነበረው ድርጅቴ አሁን ዋና ሥራውን በጊዜያዊነት በማቆም በተደረገለት ድጋፍ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን ማምረት ጀምሯል፡፡

ድርጅቴ እስከመጨረሻው ጭምብል አምራች ሆኖ አይቀጥልም ግን ይሄንን የመጣብንን ወረርሽኝ አብረን መዋጋት ስላለብን የሚያስፈልገውን ምርት እያመረትን እና እጅግ በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረብን የድርሻችንን ሀላፊነት እንወጣለን፡፡ ጎን ለጎን ደግሞ ዋናውን ሥራችንን ማስቀጠል ነው የምፈልገው፡፡” ስትል ታብራራለች፡፡የመጀመርያ እርምጃዋም የተሻለ የመስሪያ ቦታ ማግኘት እንደሆነ አክላለች፡፡

ለትራንስፖርት ምቹ ሆኖ ተመጣጣኝ የኪራይ ዋጋ ያለው መስሪያ ቦታ ማግኘት ፈታኝ ነው፡፡ አሁን ቡልቡላ አካባቢ የሚገኘው መስሪያ ቦታ ለሥራ አመቺ ነው ማለት አልችልም፡፡

በቀጣይ ሼድ ማግኘት ከቻልኩኝ እጠይቃለሁ ፡፡ ካልሆነም ግ በራሴም ቢሆን የተሻለ ዋጋ ያለው አመቺ ቦታ እፈልጋለሁ፡፡ ሠራተኞቼ ቅሬታ ባያቀርቡም ቦታው ምቹ እንዳልሆነ እረዳለሁ፡፡ ምቹ ያልሆነ ቦታ ላይ አስቀምጦ ደግሞ ጥራት ያለው ሥራ እንዲሰራ መጠበቅ ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ የመስሪያ ቦታን ችግር መቅረፍ እንዳለብኝ ይሰማኛል፡፡”

ከእነዚህ ፈተናዎች በተጨማሪ ብዙ ሰዎች የቤት ማስዋብን ሥራ እንደ ቅንጦት ማየቱ ለዘርፉ ቶሎ አለማደግ ምክኒያት እንደሆነ ትገልፃለች፡፡

የእኛ ዋና ደምበኞቻችን ድርጅቶች ናቸው፡፡ ሰው መኖሪያ ቤቱን ከፍሎ ማስዋብ ቅንጦት ይመስለዋል፡፡ ግን ለምሳሌ የማይሆን ቀለም ቀብቶ ድጋሜ የሚያስተካክልበትን፣ ሳይለካ መጋረጃው ተገዝቶ የተንጠለጠለ፣ ወይም ከቤቱ ስፋት ጋር የማይሄድ በጣም ትልቅ እቃ ገዝቶ ሁለት ሶስቴ ከመቸገር አንዴ በባለሞያ ማሰራቱ ቢለመድ መልካም ነበር፡፡

ምንም ቢሆን ግን ይሄንን ያህል መንገድ ከመጣሁ በኋላ ተስፋ መቁረጥ ሥንፍና ነውና መውደቅ እንኳ ቢመጣ መጥፎ ነገር እንዳልሆነ ደጋግሜ በማሰብ ችግሮችን በማለፍ እዚህ ደርሻለሁ፡፡

መውደቅ ጥሩ ነገር ነው የወደቀ ሰው የትኛው እንደሚያስኬደው እና የትኛው እንደማያስኬደው ያውቃል፡፡ ለምሳሌ መጀመርያ ላይ ተመርቄ እንደመጣሁ ተቀጥሮ መሥራቱ ጭራሽ የማይታሰብ ነገር ነበር፡፡ ከዛ የራሴን ከፈትኩ፡፡ አልሆነም ከሸፈ ፡፡ ከዛ ተቀጠርኩ፡፡ ደሞዜ ትንሽ ቢሆንም ብዙ ልምድ አገኘሁ፡፡ በዛላይ ደግሞ ከብዙ ሰዎች ጋር ተዋወኩበት፡፡ እና የሆነ ነገር ለመሥራት እየፈለገ ተአምር እስኪፈጠር ቤቱ ቁጭ ላለው ሰው መምከር የምፈልገው በዚህን ያህል ሺህ ብር ካልሆነ መጀመር አልችልም ብሎ ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን ዋናው ነገር ተነስቶ መንቀሳቀስ መጀመር ነው፡፡” ብላለች ሃና ዮሐንስ፡፡

ማህበራዊ ድህረ ገፅ ላይ ያጋሩ