"የሚያልሙትን ነገር ካልሞከሩ በስተቀር መሳካት አለመሳካቱ አይታወቅም ፡፡"

የጥበብን ፀጋ የሚጎናፀፉት ብዙዎች ቢሆንም ከሁሉም አይነት ግን የሚካኑት ጥቂቶች ናቸው፡፡ከሙዚቃውም፣ ከስዕሉም፣ ከተውኔቱም፣ ከሞዴሊንጉም እንዲሁም ከዲዛይኑም ጥበብ የተቸራት ማህሌት አፈወርቅ ከልጅነቷ ጀምሮ እያንዳንዱን ተሰጥኦዋን ሞክራ ስትጨርስ ልቧ አብዝቶ በወደደው የፋሽን ዲዛይኑ ላይ አረፈ፡፡

“በህልም ብቻ የሚሆን ነገር የለም ህልም ወደ ድርጊት መቀየር አለበት! የሚያልሙትን ነገር ካልሞከሩ መሳካት አለመሳካቱ አይታወቅም። ለኔ ትልቁ የጠቀመኝ ነገር ብዙ ነገር ሞክሬ የምወደውን መምረጥ መቻሌ ነው። የሚቆጨኝ ነገር የለም” ትላለች የማፊ ማፊ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ ማህሌት፡፡

“የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ ጀምሮ የማልሳተፍበት የጥበብ መድረክ አልነበርም፡፡ በተለይ ከ7ኛ ክፍል ጀምሮ ትምህርት ቤቴ ውስጥ በሚዘጋጁ የተለያዩ መድረኮች ላይ በዳንስ እና በሙዚቃ እሳተፍ ነበር፣ የቀሚስ ዲዛይኖች እየሳልኩም ለጓደኞቼ እሰጣቸው ነበር፡፡ በተጨማሪም ከጓደኞቼ ጋር የፋሽን መድረኮች እናዘጋጅ ነበር፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ዲዛይን ያደረኩት ልብስ የድሮ ዩኒፎርሜን ቀዳድጄ ነበር፡፡

ዘጠነኛ ክፍል ስደርስ ቅዳሜና እሁድ የሞዴሊንግ ትምህርት መማር ጀመርኩ፡፡ ጎን ለጎንም ከጓደኞቼ ጋር ከቤተሰብ ይሰጠን የነበረውን የኪስ ገንዘብ አጠራቅመ ሙዚቃ ሰርተናል፡፡ ሙዚቃው በተለያዩ የሬድዮ ጣቢያዎች ተቀባይነትን አግኝቶ ተደምጦልናል፡፡ ድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬ (ጆሲ)ሙዚቃውን ሰምቶ አፈላልጎ አገኘኝና ከእሱ ጋር ጆሲ ኢን ዘ ሀውስ የተሰኘውን ሙዚቃ ሰራን፡፡በጊዜው በጣም እውቅናን ያገኘ ዘፈን ስለነበር እኔንም ወደ ሙዚቃው ስራ በቀጥታ አስገባኝ፡፡

ሙዚቃው ከተለቀቀ ከ2 አመት በኋላ ቪድዮ ሊሰራ ሲያስብ የልብስ ዲዛይን እንደምሞክር ስነገረው በቪድዮ ላይ ለምንሳተፍ ሰዎች በሙሉ ዲዛይን እንዳደርግ እድሉን ሰጠኝ፡፡ እንደ ስራ ደግሞ መጀመርያ የሰራሁት ዲዛይን ይሄን ነበር፡፡ ያ የዲዛይን ስራዬ በተለይ በአርቲስቶች ዘንድ ጥሩ ትውውቅን እና ገበያ ፈጠረልኝ፡፡ ጎን ለጎንም የተለያዩ የሞዴሊንግ እና የፊልም ስራዎች እሰራ ነበር፡፡ እንዲሁም የሙዚቃ ስራዎችን አብሪያቸው እንድሰራ ከብዙ ሰዎች ጥያቄ ይቀርብልኝ ነበር፡፡
ምንም እንኳን በጊዜው የምወደውን ስራ ሁሉ የመሞከር እድሉ ቢቀናኝም ልጅ ስለነበርኩ ከሁሉም አቅጣጫ ድንገት የመጣው እውቅና ገዝፎ ከብዶኝ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡አድናቆቱና እና እውቅናው መልካም ቢሆንም ውስጤ ግን ደስተኛ አልነበረም! እንደዛ መፍጠኑን አልወደድኩትም ነበርና የተለያዩ የሙዚቃ ስራዎች ሲመጡ እየመለስኩ ለራሴ ጊዜ ሰጥቼ ምንድነው የምፈልገው? የቱ ነው የሚያስደስተኝ? ብዬ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ፡፡

ከሁሉም ሥራዎች ነፃነት የሰጠኝን የዲዛይን ስራ አጥብቄ ያዝኩ፡፡ ሁሉንም መሆን ቢቻልም ግን አብልጨ የምወደው ላይ ትኩረት ሳደርግ ስኬታማ መሆን እንደምችል ገባኝ፡፡ ይሄንን ለመወሰን ሁለት አመት ቢፈጅብኝም መጨረሻ ላይ “በቃ ማፊ ዲዛይነር ነች!” ብዬ ወሰንኩ፡፡

በጊዜው ይሰሩ የነበሩ የኢትዮጵያ የባህል ልብሶች ለሰርግ እና ለሌላ ፕሮግራም የሚውሉ አይነት እንጂ እለት ተዕለት የሚለበሱና ወጣቶች የሚመርጧቸው አለመሆናቸውን ካስተዋልኩ በኋላ ያንን ክፍተት ለመሙላት ብሎም ልብሶቹን በአለም አቀፍ ደረጃ ለማሳወቅ አቀድኩ፡፡ በአጠቃላይ በጥበብ ተሳትፎዬ በተለይ በጅማሮዬ ወቅት ከቤተሰቦቼ መካከል የምትደግፈኝ እናቴ ብቻ ነበረች፡፡ እኔ ግን “ዘርፉ ላይ ክፍተት እንዳለ ይታየኛል! ህልም አለኝ እላቸው ነበር” ፡፡

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ከጨረሰኩ በኋላ ወደ ውጭ ሀገር ወጥቼ የፋሽን ትምህርት ለመማር እድሌን ብሞክርም የትምህርት ቤቶች ውድ መሆን እና በመጠኑም ቢሆን ያልቀረው የቤተሰብ ጫና ነርሲንግ እንድማር አደረገኝ፡፡

ነርሲንግ እየተማርኩ ጎን ለጎን የዲዛይን ስራዬንም እየሰራሁ ሁለት አመት ከቆየሁ በኋላ ትምህርቱን ባልጠላውም ስራው እየጨመረ ሲመጣ ለማቋረጥ ተገደድኩ፡፡ከዚያ በኋላ ስፌት እና ፓተርን ብማርም አሁን ያለኝን የፋሽን እውቀት ያዳበርኩት ኢንተርኔት ላይ የሚወጡትን በማንበብ ነው፡፡

ይህን ስራም ስጀምር 21 ዓመቴ ነበር፡፡ እናቴ በሰጠችኝ 40ሺህ ብር መነሻ ካፒታል አንድ ማሽን ገዛሁ፡፡ በ2009 ዓም መሸጫ ሱቅም ከፈተኩ፡፡ ብቻየን እየሰራሁ ብጀምርም ቀስ በቀስ 1 ሰፊ ቀጠርኩ፡፡

ምንም እንኳን ደንበኞች ለማፍራት ባልቸገርም ዲዛይን ለማድረግ ያቀድኳቸው ቀለል ያሉ የባህል ልብሶችን ሳይሆን ሰዎች እንዲህ ይሁንልን ብለው በሚያዙት የተለመደው አይነት የባህል ልብስ ስራ ውስጥ እራሴን በማግኘቴ በድጋሜ ቆም ብዬ እንድስብ አደረገኝ፡፡

የእኔ ህልም እኔ ያሰብኳቸው ልብሶች “ማፊ” በሚባል ብራንድ ተመርተው ሰው እንደየአቅሙ እንዲገዛ ነበር፡፡ ነገር ግን ያንን ለማድረግ የሚያስፈልገው የሂሳብ አያያዝና የቢዝነስ አስተዳደር እውቀት አልነበረኝም። ቢዝነሱን የሚያስተምረኝ ሰው ስላልነበር ወደምፈልገው አቅጣጫ አልሄድ አለኝ፡፡ በዚህ ምክኒያትም የተሻለ ለመረዳት ሁለት አመት ከሰራሁበት በኋላ ሱቁን ዘግቼ አፍሪካን ዉመን ኢንተርፕረነርሺፕ ፕሮግራምን ተቀላቀለኩ፡፡

እዚህ ቦታ ደርሻለሁ ተብሎ እውቀት በቃኝ አይባልም! በተቻለ መጠን ሁሉ ከምናገኛቸው ሰዎች መማር ጥሩ ነው፡፡ የቢዝነስን ፅንሰ ሀሳብን ከማህበራቱ በመማር እና ከብዙ ስራ ፈጣሪ ሴቶች ልምድን በመቅሰም በ2011 እ.ኤ.አ እንደህልሜ “ማፊ ማፊ” የተሰኘውን ብራንዴን በመፈጠር ሌላ ሱቅ ለመክፈት በቃሁ፡፡ ዛሬ በድርጅቴ ውስጥ 55 ሰራተኞች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ 90 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ የፋሽን ኢንዱስትሪው በይበልጥ ሴቶች የሚሳተፉበት ቢሆንም የሴት ሰራተኞችን ቁጥር እንዳበዛ ያደረገኝ ምክኒያት ስራውን እንደጀመርኩ አካባቢ የሽመና ስራ የሚሰሩ ባለሞያዎች ዲዛይነር እና ነጋዴ ሳይጠብቁ እንዴት ገበያ ላይ መወዳደር እንደሚችሉ ስልጠና እሰጥ ነበር፡፡

በዚያ ወቅት ታዲያ ከነበሩ ተሳታፊዎች ውስጥ አንዲት ሴት ሸማኔ ተነስታ የልጆች እናት እና የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆኗ ቤት ውስጥ ምን ያህል ኃላፊነት እንዳለባት እንዲሁም የራሷን ዲዛይን ለመስራት ጊዜ እንደማይኖራት ነገረችኝ፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን ሰርታ ጨርሳ ከሚኖራት ጊዜ ላይ አጣብባ ለገበያ ይዛ ስትወጣ ከወንድ ሸማኔዎች እኩል ስራ ብትሰራም ገዢዎች ሴት በመሆኗ ብቻ ዋጋ እንደሚያረክሱባት ስትነግረኝ በጣም ደነገጥኩ፡፡ ማን ይገዛናል ብለው ሳይጨነቁ ገዢ እንዲኖራቸው ማድረግ አላማዬ አድርጌ ከሴት ሸማኔዎች ጋር እንድሰራ ያደረገኝ ዋናው ምክንያት ይህ ነው።

ከዚያ በኋላም ቢሆን እኔ ለሰራተኞቼ ቀጣይነት ያለው ስልጠና እሰጣችው ነበር ፡፡ ከሙያዊ ስልጠና በተጨማሪ የማደግ እና የመለወጥ ህልም እንዲኖራቸው የማበረታቻ ስልጠናዎችን ለማዘጋጀት እና የእውቀት አድማሳቸውን ማስፋት የሚችሉበት አነስተኛ ቤተመፅሀፍት ስራ ቦታቸው ውስጥ ለመገንባት አቅድኩ፡፡

ህልሜ እና ትግሌ ትልቅ ቢሆንም ዘርፉ ላይ በርካታ ችግሮች ማስተዋል ችያለሁ፡፡ ኢትዮጵያ በጥጥ ምርት ከአፍሪካ ብትታወቅም የምርት ጥራቱ ግን በዛው ልክ አላደገም፡፡ ያለማዳበርያ ያደገ ወይንም ኦርጋኒክ የሆነ የጥጥ ምርት እንደልብ አለመገኘቱ ትልቅ ፈተና ነው፡፡

እውቅና ያላቸው ያለ ማዳበርያ የሚያመርቱ ጥቂት ጥጥ አምራቾች ሀገር ውስጥ ቢኖሩም ጥጡ ፋብሪካ ከገባ በኋላ ግን በማዳበርያ ከተመረተው ጋር ይደባለቃል፡፡ አለም አቀፍ ገበያ ላይ ሲቀርብ ደግሞ መጀመርያ የሚጠየቀው “ያለማዳበርያ በተመረተ ጥጥ ስለመሰራቱ እውቅና አለው ወይ?” ነው፡፡ የውጭ ገበያ ላይ ስራዬን ሳቀርብ የሚገጥመኝ ይሄ ነው፡፡

ሌላ አገር ባሉ ዲዛይነሮች የተለመደው ነገር አምራቾችን በመምረጥ አንዱን ጥሬ እቃ ከአንድ አገር ሌላውን ከሌላ ቦታ አስመርቶ መስራት ነው፡፡ ይሄን ችግር ለማስተካከል የፈጀውን ጊዜ ይፍጅ እንጂ ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያ ውስጥ ተመርቶ ከኢትዮጵያ የሚወጣ ልብስ እንዲሆን ነው ፍላጎቴ !

ሌላው ፈተና ደግሞ የመስሪያ ገንዘብ እጥረት ነው፡፡ ባለሀብቶች እንደሌላው ሀገር ልምድ በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ መዋዕለ-ነዋያቸውን ማፍሰስ አልተለመደም ፡፡ ወጣት ስራ ፈጣሪ ተኾኖ ከባንክ ብድር ማግኘትም እጅግ ከባድ ነው፡እኔ ከጥቃቅን እና አነስተኛ ትንንሽ ብድሮችን በመበደር ነው እንደዚህ አይነት ፈተናዎችን የተወጣኋቸው፡፡”

ከዚህም አለፍ ሲል በ10 አመት ቆይታዋ የመስሪያ ቦታ ችግር እጅግ እንደፈተናት የምትገልፀው ማህሌት በመንግስት የሚሰጡ መስሪያ ቦታዎችን ለማግኘትም ያለው ሂደት ጊዜ የሚፈጅ ሆኖ ስላገኘችው በኪራይ ቤት ለመስራት መገደዷን ትገልፃለች፡፡ እንዲህ ያሉ ፈተናዎች ከዘርፉ ሳይቀረፉ የዓለምን ኢኮኖሚ ያናጋው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያም ገብቶ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆኑ እጅግ የሚያስጨንቅ ሁኔታን ፈጥሮባቸው እንደነበር ትናገራለች፡፡

“ሙሉ ለሙሉ ነበር ስራችን የቆመው፡፡የሰራተኞቼ ነገር በተለይ ደግሞ የሽመና ስራው ላይ ያሉት እጣ ፈንታ እጅግ ያሳስበኝ ነበር፡፡ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለብኝ ስለተሰማኝ መተኛት አልቻልኩም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ገና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አድርጉ ከመባሉ በፊት ኢንተርኔት ላይ ገብቼ እንዴት እንደሚሰራ እና ምን ምን እንደሚያስፈልገው ካየሁ በኋላ ቀጥታ ወደ ማምረት ገባን፡፡

መጀመርያ የተመረቱትን ጭምብሎች በጠቅላላ ለድጋፍ አዋልነው፡፡ ቀስ በቀስ መንግስትም ጭምብል መልበስን አስገዳጅ ሲያደርግ ወደ መድሀኒት እና ቁጥጥር ባለስልጣን በመሄድ የማምረቻ ፍቃድ ጠየኩ፡፡ ባለስልጣኑ ፍቃድ የሚሰጠውም ሆነ የፅዳት አስገዳጅነትን የሚተገብረው በቀዶ ጥገና ወቅት የሚደረጉ ጭምብሎችን ለሚያመርቱ እንጂ የጨርቅ ጭምብል ለሚያመርቱ የተዘጋጀ መመርያ እንደሌለ ቢገልፅልኝም ለማምረት የተዘጋጀችው ጭምብል እጅግ አደገኛ የሆነውን ወረርሽኝ ለመከላከል የሚውል እና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ስራ መሆኑን በመገንዘብ መስሪያ ቦታችንን በማጽዳት ምርት ማምረት ጀመርን፡፡ እንዲያም ሆኖ 6 ሰራተኞችን ለማሰናበት ተገድጄ ነበር፡፡ ከዋናው ምርት ገቢ በመቋረጡ ግማሽ ሰራተኞቼ ደግሞ ለተወሰኑ ሰዓታት ብቻ እንዲሰሩ ማድረግ ግድ ሆኖብኝ ነበር፡፡”

ይሄን ጊዜ በስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ትብብር ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን የመጣው ድጋፍም በከባድ ጊዜ እንደደረሰላቸው ትገልፀፃለች፡፡ በተደረገው ድጋፍ ያሏትን ሰራተኞች ከቅነሳ ከማዳን በተጨማሪ ቀድማ ማምረት የጀመረችውን ጭምብል በተጨማሪ የሰው ሀይል እና ማሽን እንድታመርት አስችሏታል፡፡

ጊዜው እና ሁኔታው ጭምብሎችን እንድታመርት ግድ ቢላትም ዓላማዋ የሆነውን የተቋቋችበት አላማ የፋሽን ዲዛይን ስራዋን ለማስቀጠል ጊዜውን እንደመዘጋጃ እየተጠቀመችበት እንደሆነ ትገልፃለች፡፡ ህልሟ ትልቅ እንደሆነ የምትናገረው ማህሌት ገበያው በድጋሜ በስፋት ሲከፈትም ከነበረችበት አድጋ እና ተሻሽላ ለመቅረብ ዝግጅት መጀመሯን ትናገራለች፡፡

“እስካሁን የመጣሁት መንገድ አብስሎኛል፡፡ ሰው የትኛውንም ያህል ተሰጥኦ ቢኖረው ካለፋ እና ጠንካራ ሰራተኛ ካልሆነ እንዲሁም ወደሚፈልገው ህልም የሚወስደውን መንገድ ተነስቶ ካልጀመረ መቼም ስኬታማ አይሆንም፡፡ ስኬት ደግሞ ግዴታ ትልቅ ገንዘብ ማግኘት አልያም ትልቅ ቦታ ላይ መቀመጥ ብቻ አይደለም! መንገድ ተነስተን ጀመርን ማለት ስኬታማ ነን ማለት ነው፡፡ ህልሜ አሁን ከያዝኩት በላይ ትልቅ ነው፡፡ ወደ እዛ የሚወስደኝን መንገድ እየተጓዝኩ ነው ያለሁት፡፡ የሚወዱት ነገር ላይ ትኩረት አድርጎ እስከመጨረሻው ይዞ መሄዱ ዋጋ አለው፡፡”

ማህበራዊ ድህረ ገፅ ላይ ያጋሩ