የኢትዮጵያ ስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ ማስተር ካርድ ፋውንዴሽንና ፈርስት ኮንሰልት በጋራ የጀመሩት ፕሮግራም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በሚያጋጥመው የምጣኔ ሃብት ቀውስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችና አዳዲስ ስራ ጀማሪዎችን የሚደግፍ የአደጋ ጊዜ መርሃ ግብር ነው ፡፡

ይህ ፕሮግራም ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ለኮቪድ19 ጫና መልሶ ማገገሚያና መቋቋሚያ ፕሮጀክት በተደረገ የ 24.8 ሚልዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ድርጅቶቻቸውን እንዳይዘጉ፣ ሰራተኞቻቸውን እንዳያሰናብቱና በአሁኑ ወቅት ያለውን ሁኔታ ያገናዘቡ የፈጠራ ስራዎችን እንዲሰሩ የሚያበረታታ ነው።

ሶስቱ ተቋማት ከባንኮች ፣ ማይክሮ ፋይናንስ እና ቢዝነስ ልማት አገልግሎት ተቕማት ጋር በመሆን በቋሚም ሆነ ጊዜያዊ ስራ ላይ ለተሰማሩ መስፈርቱን የሚያሟሉ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ በመከታተልና ሂደቱን በማስተባበር በጋር ይሰራሉ። የሚደረገውም የገንዘብ ድጋፍ መጠን እንደ ኢንተርፕራይዞቹ ስራዎቹ ፣ አይነትና ፍላጎት የሚለያይ ሲሆን የትኩረት አቅጣጫውም በሁለት ተጋላጭነት መደቦች ላይ ያተኮረ ይሆናል።

  • ከፍተኛ ተጋላጭነት ያላቸው፥ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ና ቋሚ ባልሆኑ የግል ስራዎች ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች
  • መካከለኛ ተጋላጭነት ያላቸው፥ በአገልግሎት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችና የስራ መስተጓጎል እንዲሁም የትዕዛዝ ስረዛ ያጋጠማቸው አምራች ድርጅቶች

ፕሮግራሙ በአዲስ አበባ የሚተገበር ሲሆን የሚጠበቁት ውጤቶችም

  • 24,000 አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ኪሳራ ውስጥ ወድቀው እንዳይዘጉ መከላከል
  • ከ50,000 በላይ ተቀጣሪዎች ከስራ እንዳይሰናበቱ መከላከል
  • ሶስት የፋይናንስ ተቋማት ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ያለተጨማሪ ማስያዣ የብድር አገልግሎት እንዲሰጡና አሰራራቸውንም ወደ ዲጂታል ማይክሮ ክሬዲት እንዲያሻሽሉ ማስቻል ናቸው።

የኢትዮጵያ መንግስትና የፋይናንስ ዘርፉ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚያስክትለውን ቀውስ ለመቋቋም እየሰሩ ቢሆንም፣ በሽታውን ለመከላከል አስገዳጅ የሆኑት መፍትሄዎች የሚፈጥሩት ጫና የአገሪቱን የ2012 ምጣኔ ሃብታዊ እድገት በ 2% ሊቀንሰው እንደሚችል ይገመታል። ይህ የኢኮኖሚ መዛባት ደግሞ በርካታ የስራ ዕድሎችን ስጋት ውስጥ በመጣል ስራ አጥነትን ሊያባብስ ይችላል።

ይህ ፕሮግራም ከኢትዮጵያ መንግስት የረጅም ጊዜ የስራ ዕድል ፈጠራ መርሃግብር 2013-2017 ጋር በቀጥታ የተቆራኘ ሲሆን. የወጣቶችና ሴቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የእቅዱን አፋፃፀም የሚያግዝ ነው። የዋስትና ፕሮግራሙ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በዚህ ጊዜ የሚያስፈልገውንና የሚደረገው እገዛ ላይ ያለውን ክፍተት በከፊል ለመሙላት የሚያስችል ዕድል ይፈጥራል። መንግስት ወረርሽኙ ሊያስከትል የሚችለውን ጫና ለመቋቋም የሚያደርገውን ጠንካራ እንቅስቃሴም የሚያግዝ ነው። የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ያደረገው ጥናት 1.4 ሚልዮን የቅጥር የስራ ዕድሎች ስጋት ላይ ሊወድቁ እንደሚችሉ እንዲሁም 1.9 ሚልዮን ተጋላጭ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ዜጎች በወረርሽኙ ምክንያት ከፍተኛ ገቢ ሊያጡ እንደሚችሉ ይጠቁማል።

“የኢኮኖሚ መቀዛቀዙን መቋቋም የሚያቅታቸው ኢንተርፕራይዞችና መደበኛ ያልሆኑ ቢዝነሶች ኪሳራ ውስጥ ስለሚገቡም ትኩረት ያልተሰጣቸው የማህበረሰብ ክፍሎችና ወጣቶችም ተጽዕኖ ውስጥ ይገባሉ።” በማለት ዶ/ር ኤፍሬም ተክሌ የኢትዮጵያ የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር የሁኔታውን አሳሳቢነትና የፕሮጀክቱን ጠቀሜታ ገልጸዋል።

የዚህ ፕሮግራም መበሰር ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን የ “ወጣት አፍሪካ በስራ ላይ” ስትራቴጂም ጋር አብሮ የሚሄድ ነው። “ወጣት አፍሪካ በስራ ላይ” ከወጣቶች ፣ ፖሊሲ አውጭዎች ፣ አስተማሪዎች እና ስራ ፈጣሪዎች ጋር በመመካከር የዳበረ ሲሆን በአፍሪካ 30 ሚሊዮን በኢትዮጵያ ደግሞ 10 ሚሊዮን ወጣቶች አመርቂና ጥራት ያለው ሥራን እንዲያገኙ ለማስቻል የተነደፈ ስትራቴጂ ነው።

“ወጣት አፍሪካ በስራ ላይ” ዋና አላማው ወጣቶችን ከእድሎች ጋር ማገናኘት ነው። ይህም ህይወታቸውን እንዲገነቡ ኑሯቸውን እንዲመሩ ያስችላቸዋል ፡፡ በእዚያ አጀንዳ ወደፊት ለመግፋት በመጀመሪያ እኛ የነበሩት እድሎች በኮቪድ 19 ምክንያት እንዳይጠፉ መጠበቅ አለብን ፡፡ በኋላም እነዚህ ላይ ተመስርተን መገንባት እንችላለን።” በማለት የማስተርካርድ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ዳይሬክተር አለማየሁ ኮንዴ ኮይራ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ፈርስት ኮንሰልት ከተሰኘ የግል ዘርፉን እድገት ለማሻሻል ከሚሰራ ድርጅት ጋር በመሆን በአፈጻጸም ሂደቱ ላይ የሚሳተፉ አጋዥ አካላትን ከለዩና ካሳወቁ በኋላ ለዋስትና ፕሮግራሙ ብቁ የሆኑ ኢንተርፕራይዞችን ግልጽ በሆነ መስፈርት በማወዳደር ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪው በቅርቡ ይተላለፋል።

ያጋሩት