"ነገሮች የሚሳኩት መውደቅ የማንፈራ ከሆነ ነው! ወጣት በፍፁም ተስፋ መቁረጥ የለበትም!"

ድርጅቷን ስትከፍት ንግድ እንዴት እንደሚሠራ እና እንዴት እንደሚመራ አውቆ የሚገራ አንድም ሰው በዙሪያዋ እንዳልነበር የሌዘር ኤግዞቲካ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ ሜሮን ሰይድ ታስታውሳለች፡፡

“ገና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ ነበር ወደ ንግዱ አለም የተቀላቀልኩት፡፡ ወደ እዛ የደረስኩበት መንገድም ለስኬቴ አስተዋጽዖ አድርጎልኛል፡፡ በልጅነቴ ከህፃናት ጋር ወጥቶ ከመጫወት ይልቅ ቁጭ ብሎ ማንበብ ያስደስተኝ ነበር፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ለስዕል ልዩ ፍላጎት ነበረኝ፡፡

ሰዓሊ የምሆን ይመስለኝ ነበር። በስዕል ውድድሮችም እሳተፍ ነበር፡፡ ቴሌቭዥን እና ሬድዮ ሳዳምጥ እንኳን የሆነ ጥበብ ላይ ያለ ሰው ቃለ መጠይቅ ሲደረግለት ማየት የሚያስደስተኝ ነገር ነበር።፡፡ከዚህ በተጨማሪ ቤት ውስጥ እንደ የቡና ማቅረቢያ እና የራስጌ መብራት ያሉ የእጅ ስራዎችን እሰራ ነበር፡፡

ከጥበብ ጋር የተያያዙ ነገሮችን እንደምወድ እና መንገዴ ወደ ጥበብ እንደሆነ የገባኝ በልጅነቴ ነው ፡፡ እንደማንኛውም ልጅ በትምህርቴ ጠንካራ እንድሆን ብመከርም ለምወደው ጥበብ ግን ቤተሰቦቼ በጣም ይደግፉኝ እና ያበረታቱኝ ነበር ፡፡’’

መጓዝ የምትፈልግበትን መንገድ እንደ ሜሮን ቀድሞ ለተረዳ ሰው ወደ ተፈጥሮ ሳይንስ ትምህረት ማዘንበሉ “ለምን?” ቢያስብልም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የድራፍቲንግ ቴክኖሎጂ እና ኮምፒውተር ሳይንስ ያጠናችው በህብረተሰብ ሳይንስ ውስጥ ካሉ የትምህርት መስኮች ይልቅ በተፈጥሮ ሳይንስ ስር ያሉት ወደ ምትፈልገው የጥበብ ዓለም ለመግባት የተሻለ አማራጭ ስላገኘችበት እንደሆነ ትናገራለች፡፡

“ከፍ እያልኩ ስሄድ የህንፃ ዲዛይን መማር የመማር ፍላጎት አደረብኝ፡፡ ለዚህ ትምህርት መሰረት የሚሆነውን ድራፍቲንግ ቴክኖሎጂ የተማርኩትም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ያወቅሁትን ለማካፈል ከፍተኛ ጉጉት ስለነበረኝ እሱን ተምሬ እንደ ጨረስኩ ለአንድ አመት በግል ኮሌጅ ውስጥ አስተምሬ ነበር፡፡ ያንን ሥራ ግን እንደ ቅጥር ማየት አልፈልግም! ምክንያቱም ያወቅሁትን እውቀት ማካፈሌን ማህበረሰባዊ ኃላፊነቴን እንደተወጣሁ የምቆጥረው ነው ፡፡

አንድ ዓመት ካስተማርኩ በኋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርቴን በዲግሪ መርሀ ግብር መማር ጀመረኩ፡፡ ከትምህርቴ ጎን ለጎንም ከትምህርት ቤት ጓደኛዬ ጋር ትንሽዬ ቢሮ በመከራየት ለተለያዩ ድርጅቶች መለያ አርማዎች፣ የቢዝነስ ካርዶች፣ ብሮሸሮች እና የመሳሰሉትን የግራፊክስ ዲዛይን ሥራዎች መሥራት ጀመርን፡፡
እንደልቤ እንድጠበብ ስለሚያደርገኝ ሥራውን የምሠራው በጣም ወድጄው ነበር፡፡ ትምህርት ልንጨርስ አካባቢ ደግሞ ቢዝነሳችን በጣም ተጠናክሮ ነበር፡፡’’

የሰው ልጅ የህይወት መንገድ መቀየሪያው ምክንያት አይታወቅምና የሜሮን እና ጓደኛዋ ቢሮ የነበረበት ህንፃ ላይ የፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤቷን የከፈተችው የኔክስት ዲዛይን ትምህርት ቤት ባለቤት ሳራ መሀመድ የሜሮንን የዲዛይን ብቃት እና ጥበበኛነት አስተዋለች፡፡

“ተማሪዎች ሲመረቁ የግብዣ ካርዶችን እና ሌሎች የግራፊክስ ሥራዎችን በምሠራላቸው ጊዜ አቅሜን ያየችው ሳራ ምንጊዜም ጎበዝ እንደሆንኩ ከመንገር በተጨማሪ እንድማርም ትጎተጉተኝ ነበር፡፡ ከሥራው ጋር የጊዜ መጣበቡ እንዳለ ሆኖ በገንዘብም የመማር አቅሙ እንደሌለኝ ስነግራት እሷ አስተማረችኝ፡፡ እኔም አላሳፈርኳትም አንደኛ ነበር የወጣሁት፡፡

ትምህርቴን ከጨረሰኩ በኋላ የግራፊክስ ዲዛይን ሥራውን ሙሉ ለሙሉ ለጓደኛዬ ተውኩት፡፡ከዚያም የራሴን አነስተኛ ቦታ ተከራይቼ እህቴ በገዛችልኝ 1 የስፌት ማሽን የሌዘር ቦርሳ ዲዛይንና ምርት ስራዬን ጀመረኩ፡፡
ሌዘር እኛን እየመሰለ ነው የሚሄደው! ለምሳሌ ሌዘር ጃኬት ቢኖረኝ ከሆነ ጊዜ በኋላ የእኔን የትከሻ ቅርፅ ይዞ ያንኑ ይመስለልኛል፡፡ በዛ ላይ ዘመን ተሻጋሪ እቃ ነው! አያረጅም! ልወደው የቻልኩት በእነዚህ ምክንያቶች ነው፡፡

የዲዛይን ትምህርቱም ሆነ የፋሽን መስኩ ሰፊ ቢሆንም የቆዳ ምርት ኢትዮጵያ ውስጥ በቀላሉ ሊገኝ የሚችል እና ከፍተኛ ጥራት ያለው ሆኖ ስላገኘሁት ሥራዬ አድርጌ ያዝኩት።

መጀመርያ “ኢትዮጵያ ውስጥ እንደልብ በጥራት የሚገኘው ምንድን ነው?” ብዬ አጠናሁ፡፡ ጨርቅ ቢመረትም ለአገር ከፍተኛ ጥራት ያለው ጨርቅ እንደልብ አይገኝም። ትኩረት የሚደረገው ኤክስፖርት ላይ ነው፡፡ ያለውን እንጠቀም እንኳን ቢባል እንኳን የሚገኙት ወጥ ቀለም ያላቸው ጨርቆች እንጂ ለዲዛይን ኃሳብ እና ፍላጎት ነፃነት የሚሰጡ የተለያዩ አይነት ጨርቆች ማግኘት አይቻልም፡፡

የኢትዮጵያ ቆዳ፣ በተለይ ደግሞ የደጋ በግ ቆዳ ግን በከፍተኛ ጥራት ይገኛል። ይሄ ቆዳ እንደ ጣልያን ወዳሉ አገራት ተልኮ እነሱ አንዳንድ ነገር ጨማምረውበት ተመልሶ ወደ እኛ አገር ይገባል። ይህን ሳስብ “ለምን እኛ ራሳችን ጨምረንበት ለውጭ ገበያ አናቀርበውም?” በሚል ተነሳሽነት ወደ ሌዘር ሥራ አተኮርኩ።

በሌዘር በርካታ ነገሮችን መስራት ቢቻልም እንደ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪ ውጤታማ ለመሆን በደንብ ወደማውቀው የቦርሳ ሥራ አተኮርኩ ። ሁሉንም ለመሥራት ፍላጎቱ ሳይኖረኝ ቀርቶ ሳይሆን በነበረኝ ካፒታል መስራት የምችለው አንድ ነገር ብቻ ስለነበር ነው፡፡ ለምሳሌ የሌዘር ጃኬት ብዙ ቆዳ ይፈልጋል፡፡ ጫማ ደግሞ ምርቱ መመረት ያለበት በስፋት ነው። ስለዚህ በነበረኝ አቅም መስራት የምችለውን ቦርሳ መርጬ መለያውን “ሜሮን አዲስ አበባ” ብዬ በመሰየም ምርት ጀመርኩኝ፡፡

አሁን 50 ሠራተኞች በድርጅቴ ውስጥ ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 80 በመቶዎቹ ደግሞ ሴት ሠራተኞች ናቸው፡፡ ሴት በመሆኔ ብቻ የሴቶችን ችግር ለመረዳት ቅርብ እንደሆንኩ ይሰማኛል፡፡ ሴቶች በኢኮኖሚ ጠንካራ እንዲሆኑ ስለምፈልግ ለነርሱ አብዝቼ የሥራ እድሎችን እሰጣለሁ።”

እንዲህም ሆኖ ግን በዘርፉ በርካታ ፈተናዎች እንደማይጠፉ የምትገልፀው ሜሮን ለሥራቸው የሚያስፈልጉ ጌጣጌጦች እና ተጨማሪ እቃዎችን እንደልብ ማግኘት ከባድ እንደሆነባት ትገልፃለች፡፡

“ጥሬ እቃ በብዛት እና ሁሌም አንድ አይነት በሆነ የጥራት ደረጃ ተመርቶ ማግኘት አንችልም፡፡የጥራት ደረጃው ከፍ እና ዝቅ የማይል ቋሚ የሆነ ቆዳ ማግኘት የማንችል ከሆነ እንደ አገር ያስወቅሰናል ምክንያቱም ከተዋዋልነው ውጭ ትንሽ ነገር እንኳን ብትቀየር ደግሞ በውጭ አገር ያሉ ገዥዎቻችን የተላከውን ሙሉ በሙሉ ይመልሱብናል። ያ ደግሞ ሌላ ኪሳራ ሆነ ማለት ነው፡፡ የውጭ ገበያ ላይ ማን ነች ያመረተችው ተብሎ ሳይሆን መጀመርያ የሚጠየቀው “የት አገር ነው የተመረተው?” ተብሎ ነው፡፡ እንደ አገር እነዚህ ነገሮች ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራ ይገባል ፡፡

የገንዘብ እጥረት ሁሌም ያለ ችግር ነው፡፡ አሁን ላይ በእጅ የሚቆይ ገንዘብ ባይኖርም የአንዱን ምርት ገቢ ለቀጣዩ መሥሪያ እንዲሆን እየተደረገ እንጂ የተመጣው ቢዝነስን ይዞ የሚያበድር አንድም ባንክ አላገኘሁም፡፡ የምናስይዘው ንብረት ከሌለን በቀር ከባንክ ብድር ማግኘት የማይታሰብ ነው፡፡ ባንኮቻችን ቢዝነስን እንደ መያዣ አድርገው ማበደር ቢጀምሩ በጣም ይጠቅመን ነበር፡፡ እንዲህ ያሉትን ፈተናዎች በአንድ ጊዜ መቅረፍ ባይቻል እንኳን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ለሥራ መጓተት ዋናው ምክንያትና መፍትሄ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

የመብራት መቆራረጥ ምንም ሊያሰራን አልቻለም! ትልቅ ፈተና ነው የሆነብን፡፡ የአንድ ቀን ምርት ዋጋ ማጣት ማለት በጣም ከባድ ነው። በተዋዋልንበት ጊዜ ማድረስም ይጠበቅብናል፡፡ ባለን አቅም ደግሞ ጄነሬተር ተገዝቶ በየጊዜው ነዳጅ እየተሞላ የሚሰራው ሥራ ትርፋማ አያደርገንም ። ሌላው ቀርቶ መንግስት ይህንን አይነት የመሠረተ ልማት ፍላጎቶችን ቢያስተካክልልን ትልቅ ሸክም ይቀንስልናል።” ትላለች ሜሮን ሥራዋን የሚያስተጉሉባትን ነገሮች ስታብራራ።
በንግድ ዓለም ውስጥ መክሰር ሊያጋጥም የሚችል ነገር ቢሆንም የአገር ውስጥ ገበያ ቢቀዛቀዝ በደህና ጊዜ በውጭ ንግድ ማካካስ እንደሚቻል፤ እንደ ኮሮና ቫይረስ ስርጭት አይነት አጋጣሚ ግን ሲፈጠር እጅግ ፈታኝ እና የሚያስጨንቅ እንደሆነ ትገልፃለች፡፡

“በተለይ ወረርሽኙ ወደ አገራችን እንደገባ አካባቢ እጅግ በጣም የሚያስጨንቅ ጊዜ ነበር ፡፡ የአገር ውስጥም የውጭ ገበያችንም ሙሉ በሙሉ ቆመ። የሠራተኛ ደሞዝ እንኳን መክፈል ከብዶኝ ነበር። ማድረግ የምችለው ብቸኛው አማራጭ ሠራተኞቼን በሁለት ፈረቃ እንዲሰሩ በማድረግ ግማሽ ደሞዛቸውን መክፈል ነበር። ያንን ሳደርግ ደግሞ የትራንስፖርት ዋጋ እጥፍ ሆነ፡፡ ይህ ደግሞ ሌላ ፈተና ነበር፡፡ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ሲኮን አንድም የችግሩ አካል አልያም የመፍትሄው አካል መሆን የራስ ምርጫ ነውና ድርጅታን ወዲያው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ሥራ ማምረት ጀመርን፡፡ ከመጣው ፈተና ለመውጣት በምንፍጨረጨርበት ወቅት የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ ደረሰልን።

ቀድሞ ከነበሩኝ 25 ሠራተኞች እጥፍ አድርጌ አሁን ለ50 ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር ያስቻለኝና እና የደገፈኝ ይህ ሲሆን በቂ ቁሳቁስ እና ማሸኖችን በመጨመር የጭምብል ምርቱን አስፍቼ እንድሰራም ረድቶኛል፡፡’’

ሌዘር ኤግዞቲካ የተቋቋመበት ዓላማ የሌዘር ቦርሳ ምርት ነውና ወደ ቀድሞ ቦታዋ ቀስ በቀስ ለመመለስ የውጭው ገበያ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ የምትናገረው ሜሮን እንዲህ ባሉ እና ሌሎች ፈተናዎች ተስፋ መቁረጥ እንደማያስፈልግ ትናገራለች፡፡

“ነገሮች የሚሳኩት መውደቅ የማንፈራ ከሆነ ነው፡፡ በተለይ ወጣት ተስፋ መቁረጥ የለበትም ! ጤናም ጉልበትም እውቀትም የሚኖረው በወጣትነት እድሜ ስለሆነ መሮጥ ያለብን ይሄኔ ነው። ብንወድቅም ደግሞ ራሳችንን አንስተን ድጋሜ መሮጥ ነው እንጂ ተስፋ መቁረጥ በፍፁም አያስፈልግም፡፡ በቃ ህይወት ይቀጥላል!’’

ማህበራዊ ድህረ ገፅ ላይ ያጋሩ