የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር እና ባልደረቦቻቸው በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጉብኝት እና ውይይት አድርገዋል፡፡ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ክብርት ሙፈሪሃት ካሚል ስለ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገለፃ ካደረጉላቸው በኋላ በሥራ እና ክህሎት ልማት ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኡስማን ዲዮን ኢትዮጵያ ብዙ ወጣቶች የሚገኙባት አገር እንደመሆንዋ ያላትን ሀብት በመጠቀም እንደ ግብርና እና ቱሪዝም በመሰሉት ዘርፎች ላይ ጠንክራ በመሥራት በክህሎት ብቁ የሆኑ ወጣቶችን ወደ ሥራ ማሰማራት አለባት ብለዋል፡፡የተለያዩ አገራትን የቴክኒክና ሙያ እንዲሁም የሥራ ተሞክሮ በማንሳት እና በኢትዮጵያ ሥራ እና ክህሎት ዘርፍ በሚታዩ ችግሮች ዙሪያ ከተወያዩ በኋላ የዓለም ባንክ ፣ በቴክኒክና ሞያም ሆነ ሥራን በተመለከተ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ክብርት ሚኒስትር ሙፈሪሃት በኢትዮጵያ ያሉትን አንድ ሺህ ስድስት መቶ ያህል የቴክኒከና ሙያ ተቋማት ብቁ ማድረግ፣ የሥራ ፈጠራ ሃሳብን ከትምህርት ሥርዓት ጋር ማገናኝት፣ ዕውቀትና ቴክኖሎጂን ማሸጋገር ፣ ግብርና እና ቱሪዝምን በመሰሉ እና ብዙ ሰዎችን ሊያካተቱ በሚችሉ የሥራ ዘርፎች ላይ ማትኮር እንዲሁም ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ወደ ሥራ መለወጥ የወደፊት አቅጣጫችን ነው ብለዋል፡፡ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ኡስማን ዲዮን እና ቡድናቸው ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ያደረጉትን ሁለንተናዊ ድጋፍ አድንቀው በቀጣይም በጋራ ለመስራት ላሳዩት ተነሳሽነት አመስግነዋል፡፡

ያጋሩት