የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ሙፈሪያት ካሚል የውይይቱ ዓላማ ብቁ የሆነ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የሰው ኃይል ለማፍራት ፣ የሠራተኛውን መብት የጠበቀ ጤናማ የአሠሪዎች እና የሠራተኞች ግንኙነት ለመፍጠር አዲስ ከተቋቋመው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጋር በጋራ መሥራት የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን አብሮ ለመሥራትም ሆነ አብሮ ለመኖር የታደልን በመሆናችን ያሉንን ብዙ ዕሴቶች ተጠቅመን አገራችንን በጋራ እናሳድግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሥራ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ከአሰሪዎች ኮንፌደሬሽን፣ ከውጭ አገር የሥራ ስምሪት አገናኝ ኤጀንሲዎች፣ ከሠራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን እንዲሁም ከሆቴል እና ቱሪዝም ማህበራት ለተገኙት ባለድርሻ አካላት ስለ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ገለፃ አድርገዋል፡፡ ቀደም ሲል ይገጥሙ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት እና ትኩረት የሚሹ ጉዳዩችን ለማካትት ሁሉም የበኩሉን አስተዋፃኦ ማበርከት እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡

በአሠሪና ሠራተኛ እንዲሁም ሆቴል እና ቱሪዝም ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ ጥያቄና አስተያየት ቀርቦ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ተወያዮቹ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ያጋሩት