ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 29 የሆኑ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን መሠረት በማድረግ ለአንድ ዓመት ያህል ሲዘጋጅ የቆየው
ጥናት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ዴቪድ እና ሉሲ ፓካርድ ፋውንዴሽን እንዲሁም ቢቢሲ ሚዲያ አክሽን በጋራ
በመተባበር አራት ክልሎችን እንደ ናሙና በመውሰድ ገጠር እና ከተማን አካቶ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ጥናቱን ይፋ ያደረጉት በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ
ንጉሡ ጥላሁን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአምስት አመቱ ስትራቴጂክ ዕቅዱ ላይ የሰው ሀብት ልማትን ትልቅ ትኩረት
እንደሰጠው አንስተው ይፋ የሆነው ስትራቴጂ የዕቅዱ አካል ሆኖ ወጣቶችን ማነቃቃት ፣አቅማቸውን መገንባት
እንዲሁም የህይወት እና የሥራ ምርጫቸው የተሻለ እንዲሆን የሚዲያ እና የኮሙኒኬሽን ሥራዎችን በመስራት በስነ ባህሪ
ላይ ለውጥ ማመጣት የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡ ይፋ የሆነው ስትራቴጂ ወጣቶች መረጃ እንዲኖራቸው፣ የሰለጠኑ እና
በተለያዩ አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፉ እንዲሆኑ እንደሚያግዝ በመግለፅ ግቡ የጥናቱን ውጤት መሰረት በማድረግ
ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የወጣቶች ስነ ባህሪ ላይ በስፋት መስራት ነው ብለዋል፡፡
በዴቪድ እና ሉሲ ፓካርድ ፋውንዴሽን አማካሪ የሆኑት የምስራች በላይነህ ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር
የተዘጋጅው ስትራቴጂክ ጥናት የኢትዮጵያ ወጣቶች ለሥራ እና ጤናማ ህይወት እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን ያመላከተ
መሆኑን ጠቅሰው በሥራ፣ በትምህርት ፣ ስነ ተዋልዶ ጤና እና ተሳታፊነት ላይ የጠቆማቸውን ችግሮች ለመፍታት
ስትራቴጂውን መሰረት ያደረጉ ስራዎችን በጋራ እንሰራለን ብለዋል፡፡
የቢቢሲ ሚዲያ አክሽን የኢትዮጵያ ተወካይ ሚያን መሀመድ ጁኔድ በበኩላቸው በየዓመቱ ሁለት ሚሊዮን ወጣቶች
ወደሥራው ዓለም ለሚቀላቀሉባት ኢትዮጵያ ስነ ባህሪ ላይ የሚሰሩ ስራዎች ላይ አትኩሮ ጥናት ማድረግ የተሻለ ውጤት
እንደሚያስገኝ በማስገንዘብ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ ሚዲያዎችን በመጠቀም ወጣቶች ላይ ለሚሰራው ሥራ እና ለጥናቱ
ተነሳሽነት አመስግነዋል፡፡
ጥናቱ በአገራችን ያሉ ለወጣቶች ከሥራ አመለካከት ጋር የተገናኙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ለመለወጥ መነሻ የሆኑ ግኝቶችን
ማካተቱን በመርሐ ግብሩ ላይ ከተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ዓለማቀፍ ተቋማት የተገኙ ተሳታፊዎች
ተናግረዋል፡፡

ያጋሩት