“በእኛ ሀገር ሁኔታ ወጣት እና ሴት ተኾኖ ስራ ፈጣሪነት ቀላል አይደለም! ”

የመጀመርያ ቦርሳዋን በእጇ ብቻ እንደሰፋች የምትናገረው የካባና ዲዛይን መስራች እና ስራ አስኪያጅ ሰምሃል ጉዕሽ ለስኬታማነት አላሚ፣ ተግባሪ እና ታታሪ ሰራተኝነትን ማሳያ ነች፡፡የተማረችው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህንፃ ዲዛይን ትምህርት ቢሆንም የቦርሳ ዲዛይን ፍቅር ከድሮ ጀምሮ ውስጧ እንደነበር ትናገራለች፡፡

ይሁን እንጂ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት የካባና ሌዘር ዲዛይን ሀሳብ በውስጤ ነበር፡፡ በሃሳብ ብቻም ሳይገታ ቀን ቀን ትምህርታችንን እየተማርን ጎን ለጎን ቁርጥራጭ ቆዳዎችን ከመርካቶ በመሰብሰብ ማታ ማታ ደግሞ በዶርማችን ውስጥ የእጅ እና የአንገት ጌጦችን እንስራ ነበር፡፡ እነዛን ጌጣጌጦች በስንት ብር እንሸጣቸው እንደነበር ትዝ ባይለኝም ጓደኞቻችን እና ቤተሰቦቻችን ግን ይገዙን ነበር፡፡በጣም የማስታውሰው ግን አንድ ጊዜ ወሎ ሰፈር አካባቢ ትሮፒካል ጋርደን ውስጥ የተዘጋጀ ባዛር ላይ ተሳትፈን ለመጀመርያ ጊዜ ስራችንን አሳይተን 2,500 ብር ሸጠን ነበር፡፡ ከዚያ በኃላ የመጀመርያ ቦርሳዬን በእጄ እንደሰፋሁ ትዝ ይለኛል፡፡ በነገራችን ላይ ልጅ ሆኜ አስትሮ ፊዚሲስት የመሆን ፍላጎት ነበረኝ፡፡ እኛ ሀገር ዘርፉ በቲዮሪ ደረጃ እንጂ በስፋት እየተሰራበት እንዳልሆነ ሲገባኝ አርክቴክቸርን ለመማር ወሰንኩ፡፡ አርክቴክቸር ደግሞ ለብዙ የዲዛይን ስራዎች ዓይን ይከፍታል። እኔን ይስበኝ የነበረው ግን የቦርሳ ዲዛይን ስለነበር ወደ እዚህ ዘርፍ ገባሁ”ትላለች፡፡

ከትምህርት ቤት ከወጣች በኋላ በ2009 ዓም ካባና ሌዘር ዲዛይንን ለብቻዋ ህጋዊ ድርጅት አድርጋ በአንድ ሰራተኛ ብቻ የከፈተችው ሰምሃል ስራው እንደተጀመረ እናቷ ቤት ይሰሩ እንደነበር ትናገራለች፡፡

“ተማሪ እያለን የጀመርናቸው ቢዝስነሶች በተወሰነ መልኩ ልምድ እንዲኖረኝ አድርገውኛል፡፡ ካባናን ስከፍት ነገሮች አዲስ አልሆኑብኝም ፡፡ በ300 ብር ካፒታል ነበር ድርጅቴን የጀመርኩት፡፡ ምንም አይነት የባንክ ብድርም የለብኝም፡፡ ይሁን እንጂ ድርጅቱን ከመመስረቴ በፊት ቀደም ሲል ገንብቻቸው በነበሩ ወዳጅነቶች ተጠቅሜ ሰርቼ የምከፍለው 1 የስፌት ማሽን ከመርካቶ እንዲሁም ከቆዳ አምራቾች ስራ መጀመርያ ቆዳ ተዋስኩኝ፡፡ ከዚያ እጄ ላይ ምንም አይነት ገንዘብ የለም ነገር ግን ብዙ ትእዛዞች ስላሉ እነሱን ሰርቼ የምከፍለው ቆዳ ስጡኝ ብዬ ጠየኩ፡፡ ሰርቼ መክፈል እንደምችል እርግጠኛ ስለነበርኩ ነው በድፍረት ሄጄ የጠየኩት፡፡ በኋላም መስሪያ ቦታ ስከራይም ያንን ነበር ያደረኩት፡፡ በጊዜ ሂደት የተወሰኑ ሰራተኞችን ጨመርኩ፡፡ የሚታዘዙ ትዕዛዞችን በሰዓቱ ለማድረስ ስንልም በ3 ፈረቃ መስራት ጀመርን ፡፡ ውስን ሰራተኛ፣ ውስን ማሽን እና ውስን መስሪያ ቦታ ሲኖር ጥራቱን የጠበቀ ምርት በሰዓቱ ለማቅረብ ብቸኛው በዘዴ መጠቀም የሚቻለው ጊዜን ነው፡፡ ስለዚህ ግዴታ ከፋፍለን በ3 ፈረቃ መስራት ነበረብን፡፡ አዲስ ስራ ፈጣሪ ሲኮን ያለምንም እረፍት ለመስራት ዝግጁነትን ይጠይቃል! ቀን ብቻ እየሰራሁ እድገት አገኛለሁ ብሎ ማለም የማይታሰብ ነው!” ስትል ታብራራለች ፡፡

የመጀመርያ ዙር ትዕዛዞቻቸውን አስረክበውም የ100ሺህ ብር ካፒታል እንዳስመዘገቡም ታስታውሳለች፡፡ የቆዳ ቦርሳዎችን እና ጫማዎችን በዋናነት የሚያመርተው ካባና ሌዘር 95 በመቶ የሚሆነውን ምርቱን የሚያቀርበው ለውጭ ገበያ ነው ፡፡ መዳረሻዎቹም ሩዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አሜሪካ፣ ጀርመን እና ስዊድን ናቸው፡፡

በ20ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ሆና ይህንን ድርጅት የምታስተዳድረው ሰምሃል ወጣት እና ሴት ተኾኖ ስራ ፈጣሪ መሆን ፈታኝ እንደሆነም ትገልፃለች፡፡ “በእኛ ሀገር ሁኔታ ወጣት እና ሴት ተኾኖ ስራ ፈጣሪነት ቀላል አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ የማምረቻ ኢንዱስትሪው በብዛት በወንዶች የተያዘ ነው፡፡ ከዚህ ሲያልፍ ደግሞ ወጣት ሲኾን እንደልብ ከባንክ ብድር የማግኘት እድሉ ጠባብ ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ በዘርፉ ቀድሞ የገባ/ች ወይም በስራው በደምብ ልምድ ያዳበረ/ች መካሪ ከሌለ ጉዞው የበለጠ ፈታኝ ይሆናል፡፡ አሁን የእኛ ድርጅት ካባና ሌዘር ከአረብ ሀገር የተመለሱ እና በተለያዩ የሴቶች ማህበራት ስር ባሉ መጠለያዎች ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን በመውሰድ አሰልጥነን ነው የምንቀጥረው፡፡ ድርጅታችን እስካሁን እንደ ምስራቅ አጠቃላይ የቴክኒክ እና ሙያ ማሰልጠኛ ካሉ ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል፡፡ከአጠቃላይ ሰራተኞቻችንም 80 በመቶ ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ 20 በመቶ ደግሞ ልጆቻቸውን ያለ አባት የሚያሳድጉ እናቶች ናቸው፡፡ የሴቶችን ቁጥር ያበዛነው በምክኒያት ነው፡፡ እንደ ሴትነቴ ብዙ ሴቶችን መጥቀም እችላለሁ ብዬ አምናለሁ ፡፡እንደ አምራች ድርጅት ደግሞ የሴቶች ቁጥር በእኛ ተቋም የበዛው በእኔ እምነት የምርት ኢንዱስትሪው ላይ በብዛት ለሴቶች የሚሰጣቸው ድርሻ ዝቅተኛ ሆኖ ይስተዋላል ለምሳሌ እታች ዝግጅት ክፍል ላይ ነው እንጂ ወደ ማኔጅመንት ሲያደድጉ አይስተዋልም፤ እኛ ጋር ግን ከስር ጀምሮ ቀጣይነት ያለው ስልጠና በተከታታይነት ይሰጣቸዋል፡፡ ከዛ ወደ ዲዛይን ፤ወደ ፊኒሺንግ ፤ወደ ማኔጅመንት ፤ወደ ቡድን መሪነት እና ሱፐርቪዥን እንዲሄዱ እናደርጋለን፡፡”

ለመጀመርያ ጊዜ የቀጠረቻትን ሰራተኛዋን እንደ አብነት በማንሳትም መጀመርያ በስፌት ስራ ቢሆንም የተቀጠረችው እየሰለጠነች ወደ ዲዛይን እና የፕሮዳክሽን ማናጀርነት ማደጓን አሁን ደግሞ የራሷን ድርጅት መክፈቷን ትናገራለች፡፡

“ካባና በሙሉ ኃይሉ ሲንቀሳቀስ በቀን እስከ 600 ቦርሳዎችን የማምረት አቅም ያለው ነበር፡፡ ከየካቲት 2012 ዓ.ም ጀምሮ ግን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክኒያት የወጪ ንግዱ ሙሉ ለሙሉ ቆመ፡፡ ኤክስፖርት እንደቆመ ወደ 4,000 የሚጠጉ ትዕዛዞች ናቸው የተሰረዙብን፡፡ ነገሩ ከባድ ቢሆንም ሰራተኞቻችንን በፍፁም የመቀነስ ሃሳብ አልነበረንም፡፡ለግማሾቹ ፍቃድ ብንሰጥም ያለውን ሁኔታ በመረዳት በራሳቸው ተነሳሽነት “ይሄን ያህል ደሞዝ ቀንሽና በዚህ ጊዜ ተመልሼ መጥቼ ልስራ” ያሉ ነበሩ” ፡፡ በዚያ ፈታኝ ወቅትም ምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደነበርን ስራ ዕድል ፈጠራዎች ካዩን በኋላ ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር አገናኙን፡፡ ፋውንዴሽኑ ደግሞ የራሱን ጥናት አደረገ፡፡ እንደምንለው የምንሰራ ድርጅት መሆናችንን ፣ አብዛኞቹ ሰራተኞቻችን ሴቶች መሆናቸውን እና ኤክስፖርት መቆሙ ስራችንን አዳጋች እንዳደረገብን ካጠኑ በኋላ ድጋፍ አደረጉልን፡፡ ፋውንዴሽኑ ያደረገው ድጋፍም ወደ ካፒታል የሚሄድ ሳይሆን የነበሩትን ሰራተኞች ሳይቀነሱ ተጨማሪ የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ ተጨማሪ ማሽኖችን እና ጥሬ እቃ ለመግዛት የሚያስችል ነበር፡፡ አሁን በተደረገልን ድጋፍ እያመረትን ያለነው ቦርሳ እና ጫማ ሳይሆን ለጊዜው አስፈላጊ የሆኑትን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችንና ለጤና ባለሞያዎች የሚሆኑ ልብሶችን ነው፡፡በቀን ከ3ሺህ-5ሺህ ከጨርቅ የሚሰሩ ጭምብሎችንም በማምረት ላይ እንገኛለን፡፡ ሰሞነኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዳለ ሆኖ በቋሚነት ግን በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል እንደልብ አለማግኘታችን በስራችን ላይ ከሚያጋጥሙን እክሎች መሀል አንዱ ነበር፡፡ ግን አሁን ይህን ችግር ለመቅረፍ የስልጠና ማዕከል ለመክፈት በእንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን ፡፡”

ቦርሳውንም ጫማውንም አንድ ቦታ ላይ እየሰራን ነው ፤ ከሰው ኃይል በተጨማሪም የመስሪያ ቦታ እጥረት የሚያጋጥም ነገር ግን በደምብ ከታሰበበት መፍትሔ የማያጣ ፈተና ነው ፡፡ እና የመስሪያ ቦታ እጥረት ቢኖርብንም፡፡ ለምሳሌ ብዙ የቦርሳ ትዕዛዝ ካለብን የጫማውን ቦታ ለቦርሳ በመጠቀም ነው እያመቻቸን የምንሰራው ምንም ቢሆን ግን ተስፋ አንቆርጥም” ፡፡

በ300 ብር ካፒታል ከ3 ዓመታት በፊት አንድ ሰራተኛ ብቻ ቀጥራ ካባናን የመሰረተችው ሰምሃል አሁን 131 ሰራተኞች ያሏት ሲሆን አጠቃላይ የድርጅቷ ካፒታልም 5 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡

ማህበራዊ ድህረ ገፅ ላይ ያጋሩ