“ አካሌ ለመታዘዝ አስቸጋሪ በመሆኑ እንደፈለኩ መስራት ባልችልም ሥራዬን ከመክሰም ያዳኑልኝን አመሰግናለሁ ”

ዕድሜዋ 35 ሲሆን ተወልዳ ያደገችው በባህር ዳር ከተማ ጣና ክፍለ ከተማ ቀበሌ 16 ራስ አገዝ አካባቢ ነው፡፡ እስከ 8ኛ ክፍል ተምራለች፡፡ አሁን የምትኖረው ከወንድሟ ጋር እዚያው ባህርዳር ከተማ ነው፡፡

ስንታየሁ በለጠ አሁን የምትሰራውን የሸቀጣሸቀጥ ንግድ ሥራ ከመጀመሯ በፊት በልብስ ሥፌትና ጥልፍ ሥራ ላይ ለረጅም ዓመት ስትሰራ መቆየቷን ነግራናለች ፡፡

“ በልብስ ጥልፍ እና ስፌት ሥራ ከ10 ዓመት በላይ ተቀጥሬ በሰው ቤት እሰራ ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን የምሰራው ሥራ  ለረጅም ስዓት በመቀመጥ የሚሰራ ስለነበር  እጅና እግሬ ላይ የነርቭ ህምም ችግር አጋጠመኝ፡፡ በግራ በኩል እጅና እግሬም አልታዘዝ ሲለኝ አካል ጉዳተኛ በመሆኔ ሥራውን በማቆም ለተወሰነ ጊዜ ያለ ሥራ ለመቀመጥ ተገደድኩ፡፡  ትንሽ ህመሙ ሲተወኝ  ለምን በሱቅ ውስጥ የሸቀጣሸቀጥ ሥራ አልጀምርም አልኩና ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ተመካከርን፡፡ በመቀጠልም ሥራ መሥራት አንፈልጋለን፤ ቦታ ግን የለንም በማለት የመሥሪያ ቦታ እንዲሰጠን በአካባቢያችን ወደ የሚገኝ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ቢሮ በመሄድ ጠየቅን፡፡ ከዚያም የመስሪያ ቦታ ለማግኘት መጀመሪያ መደራጀት አለባችሁ ተባልን፡፡ እኛም “ስንታየሁ በለጠ እና ቅድስት ደም መላሽ ሽርክና ማህበር” በሚል ተደራጅተን ቦታውን ከክፍለ ከተማው የጥቃቅንና አነስተኛ  ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ተረከብን፡፡

ቦታውን ማግኘት ብቻ ሥራ ለመጀመር በቂ ስላልነበረ ኮንቴነር ማሰራት ነበረብን፡፡ ሥራ ለመስራትም መነሻ ካፒታል ያስፈልጋል፡፡ ብቻ ገና ከመነሻው መንገዱ ወሰብሰብ አለብን፡፡ በጎን ንግድ ፈቃድና ሌሎች የሚያስፈልጉ ነገሮችን እያከናወንን ኮንቲይነሩን ማሰራት ጀመርን፡፡ ለኮንቴይነር እና ሌሎች ግንባታ እስከ 24000.00 / ሃያ አራት ሺህ ብር/  አውጥተናል ፡፡

ሥራ የጀመርነው በ2011 ዓ.ም ነው፡፡ የተወሰነ ጊዜ አብራኝ ከምትሰራው ልጅ ጋር ከሰራን በኋላ እሷ ሌላ ሥራ ጀመረች፡፡ እኔም ብቻዬን የሸቀጣሸቀጡን ንግድ ሥራ ያዝኩት፡፡ አሁን ከሁለት ዓመት በላይ በዚህ ሥራ ላይ ቆይቻለሁ፡፡ ቀደም ሲል ሥራውን ስጀምር ከቤተሰብና ከጓደኛኞች ገንዘብ እየተበደርኩ ዕቃዎችን አመጣና እሸጥ ነበር፡፡ የገንዘብ ዕጥረት ስላለብኝ አንዳንዴ በዱቤ አመጣና ከሽጥኩ በኋላ እመልስ ነበር፡፡ በዚሁ ሥራ ነው ቤተሰቦቼን የማስተዳድረው፡፡

በ2012 ዓ.ም ሥራችንን ደህና እየሰራን ኮረና በሽታ መጥቶ ሁሉንም ነገር እንዳልነበር አደረገው፡፡

ያንን ጊዜ ሳስታውሰው በጣም አስጨናቂና አስፈሪ ነበር፡፡ ምንም ዝግጅት ባላደረግንበት ጊዜ ስለነበር በሽታው የተከሰተው ሁሉም ነገር ቀጥ ብሎ ነበር ፡፡ በጣም አስፈሪ ነበር፡፡ እገዳዎች ሲነሱ ባለኝ አቅም ለመንቀሳቀስ ሞክሬ ነበር፤ ይህም ሆኖ ግን የገበያው እንቅስቃሴ በጣም የተዳከመ ስለነበር ፤ የዕቃዎች ዋጋ በመጨመሩ ምክንያትም ሥራችን አዝጋሚ ሆነ፡፡

እጅ ላለመስጠት ባለኝ ገንዘብ እየሰራሁ የቤት ወጭዎቼን ለመሸፈን ሞከርኩ፤ ግን በጣም ከባድ ነበር፡፡ የደረሰብኝ ጉዳት ከፍተኛ ሆኖ እንደልቤ መንቀሳቀስ የማልችል ብሆንም አካል ጉዳቴ ከመስራት ግን አላገደኝም ነበር ትላለች ስንታየሁ፡፡

ስለኮቪድ -19 ተጽዕኖ ምላሽና መልሶ ማገገሚያ ፕሮጀክት እንዴት እንደሰማችም ይህንን ብላለች፦

“በአካባቢያችን ከሚገኘው የጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ ሰዎች በስልኬ ደውለው ነገሩኝ፡፡ ከዚያም የሚያስፈልጉኝን ማስረጃዎች በመያዝ ወደ ቴክኒክና ሙያ ቢሮ በመሄድ ተመዘገብኩ፡፡ በነገራችን ላይ እዚህ ልመዝገብ እንጂ የሚያስፈልጉት መረጃዎች የሚላኩት በኢንተርኔት ላይ በተከፈተ የመረጃ ቋት ውስጥ በመሆኑ በተደጋጋሚ ወደ ኢንተርኔት ቤት በመሄድ መረጃውን ለመላክ ችያለሁ፡፡

ከተመዘገብን በኋላ ለተወሰኑ ወራት ቆይቶ ገንዘቡ በባንክ ስለገባ መጥተሸ ውሰጂ የሚል የስልክ መልዕክት ተነገረኝ፡፡ እኔም ድጋፉ እውነት ሆነ ማለት ነው ብዬ አብራኝ ከምትሰራው ቅድስት ደምመላሽ ጋራ በፍጥነት የቁጠባ ደብተሩን ይዘን ሄድን፡፡ በአካውንቱ ውስጥ 16,200.00 /አስራ ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ብር እንደገባና ማውጣት እንደምንችልም ነገሩን፡፡ እኛም ገንዘቡን በማውጣት ወደ ቤት ተመለስን፡፡ ከዚህ በኋላ ቁጭ ብለን ተነጋገርንና በገንዘቡ ምን ማድረግ እንዳለብን አወራን፡፡ እኔ በግማሹ ብር ስኳርና ዘይት በመግዛት ወደ ሱቁ አስገባሁ፤ እሷ ደግሞ በቀሪው ገንዘብ ለሱቁ የሚያስፈልጉ ዕቃዎችን አሟላችበት፡፡  የዚህ ኮቪድ -19 ተጽዕኖ ምላሽና መልሶ ማገገሚያ ፕሮጀክት ድጋፍ በጣም ነው የረዳን፡፡ቀደም ሲል ዕቃዎችን ከጓደኛ በመበደር ነበር የምናመጣው፡፡ አሁን ግን በራሳችን ገንዘብ ነው አምጥተን የምንሸጠው፡፡ ስለዚህ ድጋፉ በደንብ አግዞናል፡፡  አሁንም ቢሆን ይህንን የሱቅ ሥራ ገንዘብ ቢኖረኝ በደንብ በማስፋት የተለያዩ ዕቃዎችን በመጨመር ለመስራት አስባለሁ፡፡ ትልቁ ችግር የሆነብኝ ግን የገንዘብ እጥረት  ነው ፡፡

ከዚህ በፊት በጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ አማካኛነት አንድ ጊዜ ስለደንበኛ እና ስለገንዘብ አያያዝ ስልጠና ወስጃለሁ፡፡ ሥራዬ አነስተኛ በመሆኑ እና ብቻዬን ስለሆንኩ በተግባር አላዋልኩትም፡፡ ከዚህ የተለየ ሥራ ለመስራት ግን የአካሌ አለመታዘዝ አስቸጋሪ ስለሆነ የተሻለ ሥራ ማሰብ አልቻልኩም፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሥራችንን ከመክሰም ያዳኑልንን እንዲሁም ድጋፍ ያደረጉልንን ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ ፡፡”

ማህበራዊ ድህረ ገፅ ላይ ያጋሩ