የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ
ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዋና ዋና ተግባራት እና የሚኒስቴሩን ቀጣይ የስራ አቅጣጫ አስመልክተው ውይይት አካሂደዋል፡፡
የበጀት አመቱን ዕቅድ የተሳካ ለማድረግ የቁጥጥር እና ክትትል ስርዓቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የቋሚ ኮሚቴው
ሰብሳቢ የተከበሩ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) ገልፀዋል ፡፡
በውይይቱ ላይ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በማጠናከር ገበያ መር የሆነ የስልጠና ማዕቀፍ በማዘጋጀት እና ወጣቶችን
በማሰልጠን የልዩ ልዩ ሙያ ባለቤት እንዲሆኑ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡
ይህንንም ዕውን ለማድረግ ቋሚ ኮሚቴው የሚጠበቅበትን የቁጥጥር፣ ክትትልና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ የበጀት
አመቱን ዕቅድ አፈጻጸም የተሳካና ውጤታማ ለማድረግ ከተቋሙ ጎን መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢፌዴሪ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተበታትነው
ሲሰሩ የነበሩ ስራዎችን ለመጨረስ በሚያስችል ደረጃ በአዲስ መልክ መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡
በተቋሙ ስራን፣ ክህሎትንና የሰው ኃይልን አንድ ላይ ለማስተሳሰር ያስቻለ አደረጃጀት መፈጠሩንም ሚኒስትሯ አክለው
ጠቅሰዋል፡፡
የምጣኔ ሃብቱን ዕድገት ለማፋጠን ሚኒስቴሩ በሰው ሃብት ላይ በሥራ ባህል እና ባህሪ ለውጥ የሚታዩ የቆዩ ችግሮችን
ለመፍታት አተኩሮ ለመስራት ማቀዱንም ወ/ሮ ሙፈሪሃት አብራርተዋል ፡፡
የቴክኒክና ሙያ ስልጠናውን ከገበያ ፍላጎት ጋር በማጣጣም በአገር ውስጥና በውጭ የሥራ አማራጮችን የማስፋትና
አቅም መገንባት የሚኒስቴሩ የትኩረት መስኮች መሆናቸውንም ሚኒስትሯ አስረድተዋል።