"በትምህርት ጎበዝ መሆን ብቻውን ሥራ ፈጣሪ ለመሆን አይበቃም!"

ኃብተስላሴ የተወለደው በአዲስ አበባ ቦሌ ማተሚያ ቤት አካባቢ ነው። የ36 ዓመቱ ሥራ ፈጣሪ አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በነጻነት ብርሃን ት/ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በንፋስ ስልክ አጠቃላይ ት/ቤት ካጠናቀቀ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባውን ነጥብ አገኘ። ሆኖም በትምህርት ዘርፍ ምርጫ ወቅት በሶስተኛ ደረጃ ያስቀመጠው አፕላይድ ማቲማቲክስ ዘርፍ ስለተመደበና የትምህርት ዘርፉ እሱ ከሚያስበው የህይወት አቅጣጫ ጋር ስላልሄደለት ብዙም ሳይገፋ አቋርጦ ወጣ። ከዚያም በአድማስ ኮሌጅ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መማር ጀምሮ በሥራ ጫና ምክንያት ሳይገፋበት ቀረ።

ኃብቴ (ወዳጆቹ እንደሚጠሩት) ሥራን “ሀ” ብሎ ሲጀምር ኤ3 በሚባል የቅርብ ዘመዶቹ በሚያስተዳድሩት የማስታወቂያና የህትመት ድርጅት ውስጥ በግራፊክስ ዲዛይነርነት ነበር።

ጊዜውን ሲያስታውስ “እዚያ ለዓመት ከመንፈቅ ከሰራሁ በኋላ በገበያው ውስጥ የሚታየውን ከፍተኛ የዲዛይን ባለሙያዎች እጥረትና የክህሎት ክፍተት አስተዋልኩ። የግራፊክስ ባለሙያዎች ማስተማሪያና ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት መክፈት አስብ ነበር። ግን በቂ የገንዘብ ዝግጅት ስላልነበረኝ ለጊዜው ሃሳቡን አቆየሁት። ሃሳቡ ግን እንቅልፍ ይነሳኝ ስለነበር ለስቱዲዮ የመቀረጫ ወጪ ላለማውጣት ቤቴ ውስጥ በራሴ ላፕቶፕ የሰው እንቅስቃሴና ድምጽ በማይኖርበት ሌሊት በዘጠኝ ሰዓት እየቀረጽኩ ወጪ በማይጠይቅ መልኩ እገዛን ለማድረግ የማስተማሪያ ሲዲን በአማርኛ አዘጋጀሁ” ይላል።

“ማተሚያ ቤት ውስጥ በምሰራበት ወቅት በዘርፉ ውስጥ ያሉትን ክፍተቶች በደንብ አስተውላቸው ነበር። በተለይ በጨርቅና በልብስ ላይ የሚታተሙ ህትመቶች የሚያስወጡትን ከፍተኛ ወጪ ስመለክት መፍትሄ ማበጀት እንዳለብኝ አሰብኩ። የማተሚያ ዋጋው ከጨርቁ ወይም ከቲሸርቱ ዋጋ በጣም ይበልጥ ስለነበር ሂት ትራንስፈር ፔፐር ( Heat Transfer Paper) የተባለውን ለሥራው ግብዓት የሚሆን ወረቀት በተመጣጣኝ ዋጋ በአገር ውስጥ በጥራትና በብዛት ማምረት የሚቻልበትን መንገድ ማጥናት ጀመርኩ።”

“በጊዜውም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር ያረፉበት ወቅት ስለነበር ለቲሸርት ህትመት ይህ ሂት ትራንስፈር ፕሪንቲንግ (Heat Transfer) ወረቀት በከፍተኛ ሁኔታ ተፈላጊነት ነበረው። ለድርጅታችን መሰረት የሚሆን የፋይናንስ ብርታት ያገኘነውም በዚህ ወቅት ነበር። በቂ ዝግጅት አድርገን ወደ ሥራ ገብተን ነበር። ከመጀመሪያዎቹ አምራቾች መካከል በመሆናችን ተጠቅመናል።

“በ2003 ዓ.ም በቴሌቭዥን በሚተላለፈው የንግድ ሥራ ተሰጥኦ ውድድር ይህንኑ ሃሳብ አቅርቤ ከ40ዎቹ አሸናፊዎች መካከል ስለነበርኩ በጃክሮስ አካባቢ 80 ካሬ ሜትር የመስሪያ ቦታ በጣም ትንሽ በሚባል ገንዘብ እንደሽልማት ተሰጥቶኝ ሥራዬን አጠናክሬ መሥራት ጀመርኩ። ከዚያም በፊት 40,000 ሺ ብር ተከራይቼ ስለነበር የምሰራው ሽልማቱ ጫናውን አቃልሎልኛል” በማለት ሥራ በጀመረበት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳል።

ነገር ግን ለሕትመት የሚሆነውን ወረቀት በብዛትና ቢያመርትም የሚታተምበትን ጨርቅ ግን በፈለገው አቅርቦት መጠን ማግኘት ያልቻለው ኃብቴ ጨርቁን ለማምረት ወሰነ። ሆኖም በወቅቱ በልብስ ስፌት ሥራ ላይ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ሊሰጥ የሚችል ማሰልጠኛ ስላልነበረ አብረውት ከሚሰሩት ባልደረቦቹ ጋር በራሳቸው ሙከራ ጀመሩ። እገዛ እንዲያገኙ በማሰብ ከነሱ በፊት በሥራው ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ለማማከር ሲሄዱ ያጋጠማቸውን በዚህ መልኩ ያስታውሰዋል። “እወቀቱ ያላቸው ሰዎች ሥራቸውን የምንወስድባቸው መስሏቸው በምንም መልኩ ሊረዱን አልፈለጉም። ስለዚህ ልምድ ያላቸው ሰዎችን ቀጥረን በ2005 ዓ.ም የስፌት ሥራና ህትመትን ቀላቅለን መሥራት ጀመርን። ድርጅታችን ኃብቴ ጋርመንት የተባለው በዚህ ወቅት ነበር። በአዲስ መልክ ሥራ ከጀመርንበት ወቅት አንስቶ እስከ 2 ዓመት ድረስ በብዛት ለማምረት የጥሬ ዕቃ አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ እጥረት እያጋጠመን ተቸገርን። እንደመፍትሄ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ከውጪ ማስመጣትና መሥራት ቀጠልን። በዚህም እየተጠናከርን፣ ድርጅታችን እያደገ፣ ሥራውንም እየለመድነው መጣን። አሁን 110 ሰራተኞች አሉኝ።

ሥራችንን የበለጠ ለማስፋት ስናስብ ባደረግነው የገበያ ዳሰሳ ምቾት ያለው፣ ለጨዋታ የሚሆን የቤት ልብስ እጥረት መኖሩን ስላየን ኩርታ የተባለ የልጆች አልባሳት ዲዛይን ምርትና ሽያጭ ጀምረናል። መገናኛ፣ ገርጂና ስቴዲየም ጋር ሱቆች አሉን። ከአራስ እስከ 14 ዓመት ለሆኑ ልጆች ከ70-80 አይነት ስታይል ያላቸው ልብሶችን እናመርታለን። ጥሩ ተቀባይነትም አግኝቷል” ይላል ኃብቴ ከፈገግታና በራስ መተማመን ጋር።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ለመጀመር ለሚፈልግ ሰው ምን ትመክራለህ?” ብለን ላቀረብንለት ጥያቄ ሲመልስ “ሥራ ፈጣሪው ያሰበው ነገር ለየት ያለ ሲሆን ማህበረሰቡ ላይረዳው ይችላል። እንዲያውም ራዕዩን ሳይረዱለት በሚናገሩት ነገር በራስ መተማመኑ ሊሸረሸር ይችላል። በተጨማሪም የግብዓት እጥረት፣ ፍቃድ ለማግኘት ረዥም ጊዜ መውሰዱ ከግዢ ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ ከነዚህም ሁሉ በላይ ደግሞ ከዚህ በፊት በዚህ ሥራ ላይ ልምድ የለህም ተብሎ ዕድሎችን መነፈግ እነኚህ ሁሉ ወደኋላ ይጎትታሉ። እኔ ካጋጠሙኝ ነገሮች ተነስቼ የምመክረው አንድ ነገር ስኬት እንዳለ ሁሉ ውድቀትም ሊኖርም ይችላል። ስለዚህ ጫናን ለመቋቋም ጫንቃን ማደንደን ያስፈልጋል።

በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ድርጅታችንን በማስፋፋት ብዙ ሥራዎችን ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ነበርን። እንዲ ባሉ ጊዜያት ሥራ ፈጣሪዎች ይፈተናሉ። ይህ ሊሆን ይችላል ብሎ መገመትና ችግሮች እንደሚመጡ ቀድሞ የነገሮችን አዝማሚያ እያዩ በቂ ዝግጅት ሊያደርጉ ይገባል። ለምሳሌ እኛ ባለን ማሽን ምን አይነት ምርት ማምረት እንችላለን ብለን አስበን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ለማምረት እየተዘጋጀን ነው። ይህም ጊዜ የራሱ ፈተናዎች አሉት ግን ነገር ግን ብዙ ዕድሎችም ይዞ ይመጣል።

ኃብቴ ድርጅቱን ሞዴል በመሆን በመልካም ሥራ አፈጻጸም ወደ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝነት ስላሳደገ ከከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የዕውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቶታል።

ሥራችንን ለማስፋት ስናስብ ባደረግነው የገበያ ዳሰሳ ምቾት ያለው፣ ለጨዋታ የሚሆን የቤት ልብስ እጥረት መኖሩን ስላየን ኩርታ የተባለ የልጆች አልባሳት ዲዛይን ምርትና ሽያጭ ጀምረናል። መገናኛ፣ ገርጂና ስቴዲየም ሱቆች አሉን። ከአራስ እስከ 14ዓመት ልጆች ከ 70-80 አይነት ልብሶችን እናመርታለን። ጥሩ ተቀባይነትም አግኝቷል” ይላል ኃብቴ ከፈገግታና በራስ መተማመን ጋር።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ለመጀመር ለሚፈልግ ሰው ምን ትመክራለህ?” ብለን ላቀረብንለት ጥያቄ ሲመልስ “ሥራ ፈጣሪው ያሰበው ነገር ለየት ያለ ሲሆን ማህበረሰቡ ላይረዳው ይችላል። እንዲያውም ራዕዩን ሳይረዱት በሚናገሩት ነገር በራስ መተማመኑ ሊሸረሸር ይችላል።በተጨማሪም የግብዓት እጥረት፣ ፍቃድ ለማግኘት ረዥም ጊዜ መውሰዱ ከግዢ ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ ከዚህም ሁሉ በላይ ደግሞ ከዚህ በፊት በዚህ ሥራ ላይ ልምድ የለህም ተብሎ ዕድሎችን መነፈግ እነኚህ ሁሉ ወደኋላ ይጎትታሉ ። እኔ ካጋጠሙኝ ነገሮች ተነስቼ የምመክረው አንድ ነገር ስኬት እንዳለ ሁሉ ውድቀትም ሊኖርም ይችላል። ስለዚህ ጫናን ለመቋቋም ጫንቃን ማደንደን ያስፈልጋል። በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ድርጅታችንን በማስፋፋት ብዙ ሥራዎችን ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ነበርን። እንዲ ባሉ ጊዜያትሥራ ፈጣሪዎች ይፈተናሉ። ይህ ሊሆን ይችላል ብሎ መገመትና ችግሮች እንደሚመጡ ቀድሞ የነገሮችን አዝማሚያ እያዩ በቂ ዝግጅት ሊያደርጉ ይገባል። ለምሳሌ እኛ ባለን ማሽን ምን ማምረት እንችላለን ብለን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) ለማምረት እየተዘጋጀን ነው። ይህ ጊዜም የራሱ ፈተናዎች አሉት ግን ብዙ ዕድሎችም ይዞ ይመጣል ።”

“ሥራ ፈጠራ በትምህርት ብቻ የሚገኝ ነገር አይደለም። በቀለም ትምህርት ጎበዝ መሆን ብቻውን የራስ ሥራ ለመጀመር አይበቃም። ጥንካሬና ራዕይ፣ በራስ መተማመንና ለፈተናዎች ሁሉ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል። ሥራ መፍጠር ለየት ያለ አተያይ ይፈልጋል። በትምህርት ጎበዝ መሆን ብቻውን ሥራ ፈጣሪ ለመሆን አይበቃም። የማህበረሰቡን ችግር ለየት ባለ መረዳት ማየት ያስፈልጋል” ይላል ኃብቴ ሃሳቡን ሲያጠቃልል።

ማህበራዊ ድህረ ገፅ ላይ ያጋሩ