“ውሃ እየሸጥን ነበር የምንተዳደረው፤ አሁን ሁለት ሚሊዮን ብር ካፒታል አለኝ”
አመለ ወርቅ ተሬሳ እባላለሁ፡፡የምኖረው በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ቀበሌ 07 ልዩ ስሙ ሩዝ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡ ባለትዳርና የ7 ልጆች እናት እና የስነ ውበት ባለሙያ ነኝ፡፡ የድርጅቴ ስም ኤሚ ስፓ ይባላል፡፡ ካፒታሌ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ የምንሰራው ሥራ የወንዶችንና የሴቶችን ውበት መጠበቅ ነው፡፡ በሁለቱም ጾታ ጸጉር ቤት፣ ስፓ፣ ስቲም፣ ማሳጅና ሌሎች አገልግሎቶችን እንሰጣለን፡፡
እኖር የነበረው ከቤተሰብ ጋር ነበር፡፡ ወላጆቼ ሲሞቱ የ13 ዓመት ታዳጊ ልጅ ነበርኩ፡፡ በዚህም ምክንያት የቤቱ ውስጥ ሥራ እና ታናናሾቼን የማስተዳዳር ኃላፊነት በእኔ ላይ ወደቀ፡፡ ለቤታችን ሁለተኛ ልጅ ነኝ፡፡ አንድ ወንድምና አንድ እህት አሉኝ፡፡ የሚረዳን ስላልነበረ ገና በልጅነት አዕምሮዬ ነበር ስለ ሥራ የማስበው፡፡ ከ10ኛ ክፍል በላይ ገፍቼ መማር ያልቻኩትም በዙሪያችን ማንም ስላልነበረ ነው፡፡ ቤታችን የግል ቢሆንም በርካታ የሚያስፈልጉን መሰረታዊ ነገሮች ነበሩ፡፡ ካልሰራሁ ወንድምና እህቴን ማስተዳዳር እንደማልችል ሲገባኝ በቀጥታ ሥራ ጀመርኩ ፡፡
ይህንን ሙያ ከመጀመሪያው ጀምሮ እወደው ስለነበር አንዳንድ ነገሮችን ለመስራት የሚያስችለኝ ልምድ ነበረኝ፡፡ ባለኝ ዕውቀት ላይ በመማር ሙያውን ማዳበር ፈለኩ ፤ ለተወሰኑ ወራት ያህል የውበት አጠባበቅ ሙያ ተማርኩና ሥራውን ጀመርኩ፡፡
በነገራችን ላይ ይህንን ሥራ ከመጀመሬ በፊት ወሃ እየሸጥን ነበር የምንተዳደረው፡፡ ከነበረኝ ፍላጎትና ችግር በመነሳትም የውበት አጠባበቅ ስልጠናውን ክፍለ ጊዜ ሳልጨርስ ነበር የወንዶች የውበት ሳሎን ውስጥ ሥራውን በፍጥነት የጀመርኩት፡፡ የምሰራውም የወንዶችን እግር ማስዋብ (ፉት ማሳጅ) ነበር፡፡
እውነት ለመናገር ሥራውን ስጀምረው ከብዶኝ ነበር፡፡ የመጀመሪያዬ ስለነበር የወንዶችን እግር አጥቦ ማሳጅ ማድረግ ፈርቼ ነበር ፡፡ ግን ያው በሂደት ለመድኩት፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም ሥራውን ሰዎች ስለማያውቁት ማስለመዱም ሌላ ፈተና ነበር፡፡ ለማስለመድ ሁለት ዓመት ፈጅቶብኛል፡፡ ምንም እንኳን በሥራው የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሙኝም ከእግር ማጠብ እና ማሳጅ ማድረግ በተጨማሪ ሙሉ ሥራ ማለትም ጸጉር ማጠብ፣ ፊት መስራትና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን መስራት ጀመርኩ፡፡
ይህን ስሠራ ይከፈለኝ የነበረው በወር 700.00 /ሰባት መቶ /ብር ብቻ ነበር፡፡ ሥራውን ወድጄው እና ደስ ብሎኝ ተመችቶኝ ስለነበር የምሠራው ከደመወዙ ይልቅ ጥሩ ቲፕ አገኝ ነበር፡፡
በሥራዬ ላይ ጾታዊ ትንኮሳ ይገጥመኝ ነበር፡፡ አንዳንዴ ምርር ብሎኝ ሥራውን ለማቆም አስቤ ሁሉ አውቃለሁ፡፡ ግን ደግሞ የማገኘውን ብር ሳስብ ሥራውን መተው አልቻልኩም ነበር፡፡ እንደምንም በትዕግስት መታገል ጀመርኩ፡፡ ለ5 ዓመት ያህል ስሥራ ከደመወዜ ላይ እቆጥብ ነበር፡፡ በማገኘው የቲፕ ገንዘብም እህትና ወንድሜን እያሰተማርኩ የቤት ወጪዬንም ለመሸፈን ቻልኩ፡፡ በባንክም እቆጥብ ነበር ፡፡
በአጠቃላይ ለ5 ዓመት ያህል ይህን እየሰራሁ ከቆየሁ በኋላ አንድ ቀን አሰሪዬ ያለበቂ ምክንያት አንድ ሺህ ብር ቅጣት ጣለብኝና ተጣላን፡፡ ዕቁብ ገብቼ ስለነበር 80 ሺህ ብር ወጣልኝ፡፡ ይህንን የሚመስል የውበት ሳሎን ብከፍት እያልኩ የምቀርባቸውን አንዳንድ ደምበኞቼን አማክራቸው ነበር፡፡ እነሱም በርች አይዞሽ በማለት በሃሳብና በገንዘብ ሲያግዙኝ የዕቁቡንና በባንክ ያስቀመጥኩትን ብር ደምሬ የግሌን ሥራ ለመስራት ተነሳሳሁ፡፡
የራሴ የሆነ የውበት ሳሎን እንዲኖረኝ እመኝ ስለነበር አንድ ክፍል ቤት በመከራየት በአንድ መቶ ሽህ ብር መነሻ ካፒታል የግል ሥራዬን በ2008 ዓ.ም ሀ ብዬ ጀመርኩ፡፡ ሥራውን ስጀምር ከእኔ ውጭ ለአንድ ሰው ብቻ ነበር በጸጉር ቁርጥ የሥራ ዕድል የፈጠርኩት፡፡ ሁለት ሆነን እየሠራን ቤቱ እየተለመደ መጣ፡፡ በመቀጠልም ጽዳት የሚሰራ ሌላ ረዳት ባለሙያ ቀጠርኩ፡፡ እኔም እንዴት እንደሚሠራ ሙያውን እያስተማርኩ ከአራት ወደ 10 ሰው ቀጥሬ ማሰራት ጀመርኩ፡፡ የምሰራበት ክፍል አነሰተኛ ስለነበርም ማስፋፋት ፈልጌ ከምሰራበት ቦታ ቀጥሎ ያለውን ሌላ ክፍል በድጋሜ በ15 ሺህ ብር በድምሩ 27 ሺህ ብር ተከራይቼ የሠራተኞቼንም ቁጥር ወደ 20 ከፍ በማድረግ መሥራት ጀመርኩ፡፡
በዚህም ትንሽ ሠራሁና ሌላ ቅርንጫፍ መክፈት ፈልጌ ሳስብ ብር አነሰኝ፡፡ የመንግስት ሰዎች ከጥቃቅን ቢሮ በመምጣት ደርጅቴን ሲጎበኙ ተገርመው ሥራዬንና ቤቴን በማየት አበረታቱኝ፡፡ ከዚያም እንዴት እንደሚያግዙኝ አወራን፡፡ ቁጠባ ቆጥቢ አሉኝ፤ እኔም 20 በመቶ ቆጠብኩ፡፡ ከዚያ ከባንክ ብድር ተመቻቸልኝ፡፡ አንድ መቶ ሽህ ብር ተበድሬ የሚያስፈልገኝን የመሥሪያ ዕቃ ገዝቼ ጨመርኩ፡፡ አራት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከሁለት ክፍል ወደ 3 ክፍል ቤቱንም አስፋፋሁት፡፡ ጥሩ የውበት ሳሎን ሆነ፤ ከሌሎችም ጋር ጥሩ የሚባልና ተወዳዳሪ ድርጅት ሆነልኝ፡፡ የሠራተኞቼም ቁጥር ከፍ አለ፡፡ በዚህ አጋጣሚ የተባበሩኝን ሁሉ አመሰግናለሁ፡፡
ሥራ ማለት ለእኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ የሰው ልጅ ሲኖር መሥራት አለበት፡፡ማንም ሰው የሰውን እጅ ማየት የለበትም ሥትሰራ ነው ማንም የሚፈልግህ፤ ማንም ሰው ተቀምጦ የፈለገውን ማግኘት አይችልም፡፡ በሥራ አምናለሁ ፤ ወንድሜ እንኳን ቢመጣ መሥራት እየቻለ ቁጭ ብሎ እሱን መርዳት አልፈልግም፤ መሥራት ስላለበት፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ነው ስለፋ የነበረው እና ሥራ ለኔ ክቡር ነው፤ ካከበርከው ያከብርሃል፡፡ የሠው ልጅ የሆነ ነገር ለማግኝት ብዙ ዳገቶችን መውጣት መውረድ አለበት፡፡ሥራ መምረጥ የለብንም፤ ዝቅ ብሎ መሥራት ክብር ነው፡፡
አሁን ድርጅቴ 3 ቅርጫፎች አሉት፡፡ በድምሩ ከ40 በላይ ሠራተኞችን አስተዳድራለሁ ፡፡ የወንድ ሠራተኛ ብዛት 10 ሲሆን ቀሪዎቹ 30 ሴቶች ናቸው ፡፡
ኮቪድ -19 በሽታ በተከሰተ ጊዜ ምንም የንግድ እንቅስቃሴ አልነበረም፡፡ ደንበኞቻችን ከቤት አይወጡም፤ በሽታው በንክኪና በትንፋሽ በፍጥነት የሚተላለፍ በመሆኑ ሰዎች አገልግሎት ዘርፍ ላይ መጥተው ለመጠቀም አስቸጋሪ ነበር፡፡ ለሳምንታት ድርጅቱን ዘግተናል፡፡ ገቢያችን በጣም ሞቶ ነበር፡፡ እንዳውም በከተማችን አንድ ታዋቂ ዶክተር በኮቪድ ይያዛል፡፡ የእኛ ደንበኛ ስለነበር ሰው ወደ ድርጅታችን እንዳይመጣ ከተማው ውስጥ ይወራ ነበር፡፡ በዚህ ራሱ በርካታ ደንበኞቻችን ወደ እኛ መምጣት አልቻሉም ነበር ፡፡ ቢሆንም ግን ሥራ ጀምሩ በተባለ ጊዜ አልኮል፣ ሳኒታይዘር፤ ጓንት ፣ማስክ በመግዛት መልሰን ሥራችንን ጀመርን፡፡ ያም ሆኖ ግን በጣም ከባድ ነበር፡፡ ለሠራተኞቼ ደመወዝና የቤት ኪራይ የምከፍለው ከባንክ ገንዘብ እያወጣሁ ነበር ፡፡ ሠራተኞቼን በሽፍት አስገባ ነበር፡፡ በሰዓቱ 23 ሠራተኞች ነበሩኝ፡፡
ተዘግቶ በተከፈተ ጊዜም ቢሆን ሥራውን እንደገና ለመጀመር ደንበኛ ለማምጣት በጣም ተቸግረን ነበር፡፡ በዚያ ላይ ለአንድ ቤት ብቻ 27,500 /ሃያ ሰባት ሽህ አምስት መቶ/ ብር በወር እከፍል ስለነበር አከራዩ የቤት ኪራይ ሊተውልን ቀርቶ ሊቀንስልንም አልቻም፡፡ ኪራዩንም ቀስ ብዬ እንድከፍል ብለምነው አይቻልም አለኝ፡፡ ኮቪድ -19 ከተከሰተና በከተማችን ውስጥም እንደ አገር ሁሉም ነገር ሲዘጋጋ ሥራ ከመጥፋቱ የተነሳ ደበንበኞች እንዲመጡ ስልክ እንደውል ነበር፡፡ ሥራው በጣም ተቀዘቅዞ ስለነበርና ሠራተኞችን ላለመበተን፡፡ አንድ ቀን ቀደም ሲል ብድር የተበደርኩበት ባንክ ሂጄ ሰለብድሩ የመመለሻ ጊዜ ማለፍ ስጠይቅ የብድሩን መክፈያ ጊዜ አራዘሙልኝ፡፡ ከዚያም ከብዙ ድካምና ልፋት በኋላ ሥራችንን በመቀጠል ገቢያችን የበፊቱን ያህል ባይሆንም አሁን እየሰራን የደረስንበት ደርሰናል፡፡ አሁን የምሰራበትን ክፍል የተከራየሁት በ35 ሺህ ብር ነው፡፡
የኮቪድ -19 ተጽዕኖ ምላሽና መልሶ ማገገሚያ ፕሮጀክት እንዳለ የሰማሁት በቴሌቪዥን ነበር፡፡ ከዚያ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዝ ቢሮ ስልክ ተደውሎ በኮቪድ 19 በሽታ ምክንያት ንግዳቸው ለተጎዳ ሰዎች የመጣ ድጋፍ አለ ብለው ነገሩኝ፡፡ በሰዓቱ ደስ ነው ያለኝ፡፡ ለምን ሥራችን የተጎዳና ገቢያችን እንደ በፊቱ ባለመሆኑ እንዲሁም በነበሩብን ሌሎች ችግሮች ምክንያት ገንዘቡ አስኪመጣ ቸኩዬ ነበር፡፡ ከመጣ በኋላ የሚጠይቀውን መስፈርት አሟልቼ ተመዘገብኩ፡፡ ከዚያም የሚጠበቅብኝን ዶክመንት ሞባይሌን ተጠቅሜ በኢንተርኔት ላኩ፡፡ ከወራቶች በኋላ ገንዘቡ እንደመጣ እና አዲስ የቁጠባ ደብተር ከፍቼ ማውጣት እንደምችል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስልክ ተደውሎ የተፈቀደልኝን 75,000.00 /ሰባ አምስት ሺህ ብር እንድወስድ ነገሩኝ፡፡ ሠራተኞቼን እንዳልቀንስ ገንዘቡ በጣም ነው የጠቀመኝ፤ የተበደርኩትንም መክፈል ቻልኩ፡፡
ከብድር ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ ለማኑፋክቸሪንግ ሥራ ብድር ይሠጣል፡፡ በአገልግሎት ዘርፍ ላይ ለተሰማራን ደግሞ ድጋፍ እና ትብብር ስለማይደረግ ችግር ገጥሞኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይቺ ልጅ ጎበዝ ሰራተኛ ናት፤ ሴት ናት ፤ ተሸላሚ ናት ብሎ ብድሩ እንዲሰጠኝ ላደረጉ ሁሉ አመሰግናለሁ፡፡ በሰዓቱ የተበደርኩት ከ1.3 ሚሊዮን ብር በላይ ነበር፡፡ እየከፈልኩ ነው፡፡
ሌላው እንደ ችግር አየገጠመኝ ያለው ነገር ቦታ ነው ይህንን መንግስት ሊፈታልን ይገባል፡፡ ተከራይቼ ነው የምሰራው፡፡ ቦታ ቢሰጠኝ ግን ድርጅቴን በማስፋፋት ለበርካቶች የሥራ ዕድል መፍጠር እችላለሁ፡፡