“ዓለም ስለ አፍሪካ በተለይም ደግሞ ስለ ምስራቅ አፍሪካ የሚሰጠው የወረደ ግምት እኔንና ጓደኛዬን ጃዋድን ዘወትር የሚያሳስበን ጉዳይ ነው።”

“ ዓለም ስለ አፍሪካ በተለይም ደግሞ ስለ ምስራቅ አፍሪካ የሚሰጠው የወረደ ግምት እኔንና ጓደኛዬን ጃዋድን ዘወትር የሚያሳስበን ጉዳይ ነው። የዛሬ አስር አመት ገደማ ለንደን በሚገኘው ቤታችን ቁጭ ብለን ስለዚሁ ጉዳይ እንደሁልጊዜው በምንወያይበት ጊዜ ይህን የተሳሳተ ግምት ለማስቀየር የሚያስችለንን የስራ ሀሳብ አፈለቅን፡፡ እሱም በአፍሪካውያን ከአፍሪካ ተመርተው ለዓለም ገበያ የሚወጡ ቅንጡ ጫማዎችን መስራት ነበር፡፡”ይላል አዛሪያ ስራ ስለጀመረበት ወቅት ሲያስታውስ።

እኔና ጓደኛዬ በትምህርት እና በስራ የመጣንበት መንገድ ለየቅል ቢሆንም ይሄ ሀሳብ ግን አንድ አደረገን፡፡ እኔ በአሜሪካ ሀገር ተወልጀ እድገቴ ደግሞ በኬኒያ ነበር፡፡ ከዚያም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ተወለድኩበት አሜሪካ ተመለስኩ፡፡ከዚያም የከፍተኛ ትምህርቴን እዛው አሜሪካን ጨርሼ ወደ ስራ ገባሁ፡፡”

ህይወት ወደ እንግሊዝ ለንደን የወሰደው አብሮ አደግ ጓደኛው ጃዋድ ደግሞ ከታዋቂው ለንደን ስኩል ኦፍ ፋሽን ተመርቆ በጫማ ዲዛይን እና ምርት ላይ መስራት ጀምሮ እንደነበር አዛሪያ ያስታውሳል፡፡

“ከጊዜያት በኋላ ስሰራበት የቆየሁት መስሪያ ቤት ለንደን ወደሚገኘው ቢሮዋቸው አዘዋወረኝ፡፡ እዚያም ጃዋድን በድጋሚ አገኘሁት፤ አብረንም መኖር ጀምርን፡፡ አብረን በምንኖርበት ጊዜ አብዛኛውን ጊዜያችንን ሰዎች ስለ አፍሪካ በተለይም ደግሞ ስለ ምስራቅ አፍሪካ ያስቀመጡትን የወረደ አመለካከት እና የሳሉትን አሉታዊ ገፅታ እንዴት ማስተካከል እንደምንችል እንወያይ እና ሀሳቦችን እናፈልቅ ነበር፡፡

ያኔ ነበር አሁን የምንሰራበትን ኤንዚ የተባለው መለያችን እንዴት እንዲሰራ እንደምንፈልግ ሀሳቡን ያፈለቅነው፡፡ ኤንዚ በጭንቅላታችን ውስጥ ያለ እንጂ በመሬት ላይ የወረደ ሃሳብ አልነበረም፡፡ “ሙሉ በሙሉ በአፍሪካ የሚመረት የቅንጦት ምርት ነው መሆን ያለበት! “ ብለን ስንወስን እኔ በግሌ የሚሆን አልመሰለኝም ነበር፡፡ እንደዚያ ጥራት ያለው ምርት አፍሪካ ውስጥ ማን አቅም ኖሮት ሊያመርት ይችላል ብዬ እራሴን እጠይቅ ነበር፡፡

ከዚያ በ2002 ዓ.ም ሌላ ንግድ ለመጀመር እኔ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ቆዳ ጥራት የሰማው ጓደኛዬም እግረ መንገዴን ጥናት እንዳደርግ የቤት ስራ ሰጥቶኝ ነበር፡፡ የቤት ስራዬን ስጨርስ ጓደኛዬን ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ አደረግሁት፡፡ የተለያዩ ቆዳ ፋብሪካዎችን ጎበኘን፡፡ ባየው የቆዳ ጥራት እና የዋጋ ተመጣጣኝነት እጅግ ተደነቀ ፡፡ ያን ጊዜ ኤንዚን በጭንቅላት ውስጥ ከተቀመጠ ሀሳብነት አውጥተን መሬት ለማውረድ ወሰንን፡፡ ያሰብነውን ለመስራት ከወሰንን በኋላ ቀጣዩን አንድ አመት ዲዛይኖቻችንን በምንፈልገው የጥራት ደረጃ የሚያመርትልን ምርጡ የቆዳ ፋብሪካ የቱ እንደሆነ በማጥናት አሳለፍን፡፡ ፋብሪካውን ካገኘን በኋላ ምርታችን እኛ በምንፈልገው ጥራት ደረጃ ልክ እንዲመረት ለማዳበር ሌላ አንድ አመት ፈጀብን ። ሆኖም ገበያ ላይ ስናቀርበው 55 በመቶ ያህል ተቀባይነት አላገኘም ነበር፡፡
ስራችንን በማሻሻል ተቀባይነቱን ለመጨመር ብንሞክርም አልተቻለም፡፡ ስለዚህም ቀጣዩን 4 አመታት በ3 የተለያዩ ፋብሪካዎች ጋር ምርታችንን ለመሞከር ተገደድን፡፡

ከ5 አመታት ሙከራ በኋላ “የልፋታችንን ያህል ለዓለም ገበያ የምናቀርበው ጥራቱን የጠበቀ የቅንጦት ጫማ ማግኘት ያልቻልነው ለምንድን ነው? እንዲህ ያለውስ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ መሰራት ይችላል?” የሚል ክርክር በመሀላችን ተፈጠረ፡፡ከዚህም አልፎ ተስፋ እስከመቁረጥ አድርሶን ነበር፡፡ በክርክራችንና በውይይታችን መሀል በትንሽዬ ቦታ እና በነበረን አቅም ጫማዎቹን እራሳችን መስራት የምንችልበትን ሀሳብ አፈለቅን፡፡

ከዚያም በ2008 ዓም በ 1,000 ዶላር መነሻ ካፒታል ትንሽ ቦታ ተከራየን እና የማምረቻ ፍቃድ አውጥተን በሁለት ሰራተኞች ብቻ ሥራ ጀመርን፡፡

መጀመርያ 20 ጫማዎችን አመረትን፡፡ እነዚያ ጫማዎች ከጥራት ጥግ የራቁ ቢሆኑም ባለፉት አመታት ከሌሎች ፋብሪካዎች ጋር ለማምረት ስንሞክር ከነበሩት እጅግ የተሻሉ ነበሩ፡፡

ያጠራቀምነውን ገንዘብ በጠቅላላ ቀድሞ ስንሞክርበት በነበሩ ያልተሳኩ ምርቶች ላይ በማባከናችን የእራሳችን ማምረቻ ላይም የሚፈልገውን ያህል መዋለ ነዋይ ለማፍሰስ አልቻልንም ነበር፡፡በመጨረሻም ግን ሁሉም ነገር በራስ ያምራል እንዲሉ በተለይ ባለፉት 3 አመታት ትልቅ ለውጥ ማምጣት ችለናል፡፡ ለውጡ እስኪመጣ ግን በጣም ፈታኝ ጊዜ ነበር ያሳለፍነው፡፡ ካሰብነው ጊዜ በላይም ፈጅቶብናል፡፡ይሁንና ግን ከአቋማችን አለመዋዠቃችን ኩራታችን ነው፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ያኔ በሀሳባችን ልንገነባው ያሰብነውን አይነት ድርጅት አሁን መገንባት ችለናል፡፡

አፍሪካን በተሻለ መልኩ ለማስተዋወቅ አቅደን ስንነሳ እርግጥ ይህንን ለማድረግ በርካታ ስራዎች ቢኖሩም የፋሽን ዘርፉን ፣ በተለየም ደግሞ የጫማ ምርትን የመረጥንበት ምክኒያት ጓደኛዬ እና የስራ አጋሬ ጃዋድ የጫማ ዲዛይነር በመሆኑ ነበር፡፡’’ ይላል አዛሪያ፡፡

“ጫማ ማረት ቀላል አይደለም። የኢትዮጵያን የምርት ብቃት ማሳየት ከፈለግን ግን ከባዱን ነገር መምረጥ ነበረብን ፡፡ አሁን 45 ሰራተኞች አሉን፡፡ድርጅቱ ምርቶቹን ወደ አሜሪካ አውሮፓ እና ሆንግኮንግ እየላከ ይገኛል፡፡ በሌላ የዓለም ሀገራት አምራች ለመሆን ሲታሰብ እሱ/እሷ/ ጎበዝ የሆኑበትን እና የሚቻላቸውን ነገር እየሰሩ ሌላውን ነገር በውጭ ፣በሌላ አምራች ማሰራት ነው የተለመደው:: እሱን አስበን መነሻችን ላይ ብንፈተንም ለእኛ በተቃራኒው ሙሉ ነገሩን እራሳችን ማምረት ሰርቶልናል፡፡

በዘርፉ ላይ ካጋጠመን ችግር መሀል ብቃት ያለው አጋር አምራች ማግኘት ዋናው ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ጥሬ እቃዎችን ሀገር ውስጥ ማግኘት ፈታኝ ነበር፡፡ እነዚህን እቃዎች ከውጭ ማስመጣት ደግሞ ካለን ትንሽ አቅም ጋር ሊጣጣም አልቻለም፡፡ በዚህም ምክንያት ስራችንን ለማከናወን ከብዶን ነበር፡፡

በተጨማሪም ምንም እንኳን ባለንበት የፈረንጆቹ አመት ለመጀመርያ ጊዜ ትልቅ ትርፍ ለማግኘት አቅደን የነበረ ቢሆንም ያልጠበቅነው ነገር ዱብእዳ ሆኖ የኮሮና ቫይረስ ወረርሸኝ በመከሰቱ እጅግ ስራችንን ጎዳው፡፡ የውጭ ገበያው ሙሉ በሙሉ ተዘጋ፡፡ ምርታችንም ሙሉ በሙሉ ቆሞ ነበር፡፡ ትርፉ ቀርቶ ጭራሽ ሰራተኛ ለመቀነስ ተገድደንም ነበር፡፡
እንዲህ መንገዳገድ ላይ በነበርንበት ወቅት ታዲያ ከተፍ ያለው የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ የቀሩ ሰራተኞችን እንዲጠብቁ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ሰዎች እንዲቀጠሩ እና አዳዲስ ማሽኖችን ገዝተን ወቅቱ የሚያስፈልገውን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማምረት እንድንጀምር ረድቶናል፡፡ ጭምብሉ ድርጅታችን ሲያመርት ከቆየው የምርት አይነት እጅግ የተለየ ቢሆንም ድርጅቱን ከድንገተኛ ውድቀት ከመታደጉም ባለፈ የተፈጠረውን ችግር ለመርዳት አስችሎናል፡፡ ማህበረሰባዊ ኃላፊነታችንንም እንድንወጣ አድርጎናል፡፡

ከቅርብ ወራት ወዲህ በዓለም አደባባይ የተጀመረው የጥቁሮች ህይወት ዋጋ አለው የሚለው እንቅስቃሴ በመጠኑም ቢሆን በዓለም ገበያ ለቀረቡ ጥቁር አምራቾች ድጋፍ እያስገኘ ነው፡፡በዚህ ንቅናቄ ምክንያትም ገበያው በመጠኑም ቢሆን መንቀሳቀስ መጀመሩ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡

በዚህ እኛ በመጣንበት መንገድ ያጋጠሙንን ፈተናዎች ሁሉ በፅናት አልፈን ዛሬ ላይ መቆማችን ትልቅ ጥንካሬ ሆኖናል፡፡ እኔም ብሆን ያለ ቤተሰብ ድጋፍ እዚህ አልደርስም ነበር፡፡ የስንቶቻችን ቤተሰቦች ናቸው አስር አመት ሙሉ ስንታገል እና ስንወድቅ እያየ ተመልሰን እንድንነሳ ያለመታከት አጠገባችን ቆመው የሚደግፉን? በዚህ ረገድ በጣም እድለኛ ነኝ፡፡ እናም ከጎኔ የነበሩትን ቤተሰቦቼንና ያገዙኝን ሁሉ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡”

ማህበራዊ ድህረ ገፅ ላይ ያጋሩ