"ስራ ፈጣሪ ማለት በሚቻለው መንገድ ብቻ የሚሄድ ሳይሆን በማይቻለውም ማለፍ የሚችል ነው!"

ዛሬ ሙሉ ለሙሉ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የቆዳ ቦርሳዎች አምራች ድርጅት ባለቤት የሆነው ዳንኤል ታደሰ ትናንት የቱንም አይነት ስራ ሳይንቅ ማደጉ ለዚህ እንዳበቃው ይናገራል፡፡

የ40 አመቱ ዳንኤል ስራ መስራት የጀመረው የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ከጨረሰ በኃላ ሳይሆን ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በመኖርያ አካባቢው ያሉ ስራዎችን በመስራት ነበር፡፡

“ህይወቴን ያሳለፍኩት በብዙ ሞያዎች ውስጥ ነው፡፡ ጋራዥ ውስጥ ሰርቻለው፡፡ የእንጨት ስራም እሰራ ነበር፡፡ ምንም አይነት ስራ ቢሆን ሳልንቅ ከትምህርቴ ጋር ጎን ለጎን እሰራ ነበር፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ በስራ እንዳድግ ያደረገኝ የኑሮ ሁኔታችን ዝቅተኛነት ቢሆንም የስራ ፍቅር እና የመለወጥ ጉጉት ወትሮም ውስጤ ነበረ ፡፡ ነገር ግን የትኛውንም አይነት ስራ ለመስራት እና ለመለወጥ አእምሮዬ ክፍት ስለነበረ የስራ ፍቅር አብሮኝ አድጓል፡፡”

ከተመረቅሁበት የትምህርት ዘርፍ በተለየ ዘርፍ ላይ ስራ ፈጣሪ የሆነኩበትም ምክኒያት ለየትኛውም ስራ አእምሮየን ክፍት ማድረጌ በፈጠረው በጎ ተፅዕኖ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፖፑሌሽን ሪሶርስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት 2ኛ ዲግሪ ድረስ ተምሬያለሁሁ፡፡ ለተወሰኑ አመታትም ተራድዖ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሬ ሰርቻለሁ፡፡ ትልቁን የስራ ፈጣሪነት ልምድ እና እውቀት ያገኘሁትም በተለያዩ ኮሌጆች የአንተርፕረነርሺፕ እና ቢዝነስ ማኔጅመንት ትምህርቶቸን በማስተምርበት ወቅት ነበር ፡፡”

ዳንኤል የልብ ጓደኛው ከሆነው አዱኛ ጋር በመሆን በቲዮሪ ጠንቅቀው የሚያውቁትን የስራ ፈጠራ እውቀት እንዴት ወደ ተግባር መቀየር እንዳለባቸው ሁሌም ያስቡ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

“በእርግጥ ስራ ፈጣሪነት የሚለው ሀሳብ ሁሌም ውስጤ የነበረ ነገር ነው ፡፡ከጓደኛዬ ጋር በምንገናኝበት ጊዜም “ምን እንስራ ? ምን እንፍጠር? እንዴት ነው ወደ ራሳችን ስራ መግባት የምንችለው? ሀገር ውስጥ ያለው ጥሬ ሀብት ምንድን ነው? እንዴትስ ነው ያንን ለውጠን ገበያ መፍጠር የምንችለው? ሀገራችንንም ማስተዋወቅ የምንችለው” እያልን እንነጋገር ነበር፡፡

በቆዳ ምርት ዘርፍ ላይ ብዙ የሚሻሻሉ ነገሮች እንዳሉ አስተዋልን፡፡ መጀመርያ የወሰድነው እርምጃ ግንኙነቶችን መፍጠር እና ማጠናከር እንዲሁም ሊያግዙን የሚችሉ ሰዎችን መፈለግ ነበር፡፡ ካለን የስራ ፍቅር እና ፍላጎት አንፃር ዘርፉ ላይ ቢንገባበት ለውጥ ማምጣት እንደምንችል አመንን፡፡ ከዚያም የቆዳ ቦርሳዎችን እያመረትን ሙሉ ለሙሉ ለውጭ ገበያ የሚያቀርበውን ኮት ኬት ኃ/የተ/የግ/ማኅበርን እ.ኤ.አ 2016 ዓ.ም መሰረትን፡፡ “እኛ ይሄንን መስራት እንችላለን! ሰርተን ደግሞ ስራ መፍጠር እንችላለን!” ብለን ከኛ ጋር ደግሞ ማን አብሮን ሊሰራ ይችላል የሚለውን ማሰብ ነበር፡፡ ሁለታችንም ኤን ጂ ኦ ውስጥ ሰርተን ነበር እና እዛ የነበሩ ፕሮጀክቶች ላይ በተለይ ሴቶች ስራ ፈላጊዎች ብዙ እንደሆኑ እናውቃለን፡፡ ስለዚህ ለእነሱ የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ለመፍጠር በማሰብ የሥራ ዕድል ፈጥረን፡፡ በ3 ሰራተኞች የተጀመረው ኮት ኬት አሁን 62 ሰራተኞች ያሉት ሲሆን 95 በመቶ ያህሉ ደግሞ ሴቶች ናቸው፡፡

የምርት ስራው ላይ ብቻም ሳይሆን የአስተዳደር ስራዎቻችንም ላይ ድርጅታችን ውስጥ የሚሰሩት ሴት ሰራተኞች ናቸው፡፡ ኮት ኬትን በዙሪያችን ካሉ ሰዎችና ከራሳችን ኪስ በማዋጣት በ20ሺህ ብር መነሻ ካፒታል ነበር ሀ ብለን ያቋቋምነው፡፡ሁለት ማሽን ብቻ ነበረን፡፡ መስሪያ ቦታ ደግሞ፡፡ በኪራይ ነበር፡፡ እንደተጀመረ አካባቢ ሁሉም ነገር በጣም የሚያስጨንቅ ነበር፡፡ ዋናው ነገር ግን በስራው ማመን እና ድፍረት ነው፡፡ እንደውም ከነአባባሉ “የነብርን ጭራ አይዙትም ከያዙትም አይለቁትም” ይባላል፡፡ ስራ ለመጀመር መጠባበቅ ያለብን ምንም አይነት ምቹ ሁኔታ የለም! ያለንን ነገር ይዘን ነው በድፍረት የገባነው፡፡ ከዛ እኛም እየተስተካከለን እና እየተቀረፅን እንሄዳለን እንጂ “እነዚህን ነገሮች ሳሟላ ነው የምጀምረው” አይባልም፡፡ እውነት እንነጋገር ከተባለ ደግሞ እንኳን ስንጀምር ይቅርና አሁንም ሁሉም ነገር ሙሉ አይደለም፡፡ በስራ ፈጣሪነት አለም ውስጥ ሁሌም ውጣ ውረድ እና ፈተና አለ፡፡”

“ስራ ፈጣሪነት ማለት በሚቻለው መንገድ ብቻ ሳይሆን በማይቻለውም ማለፍ መቻል ነው፡፡ የቆዳ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሰፊ ሰንሰለት ያለው በመሆኑ ከስር ጀምሮ በሚፈጠሩ ግድፈቶች ምክኒያት ጥራቱን የጠበቀ ሌዘር ማግኘት አለመቻሉ በዘርፉ የሚያጋጥም ዋና ተግዳሮት ነው፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ያለቀለት ሌዘር ማግኘት በጣም ፈታኝ ነው ፡፡ እኛ ጋር ከመድረሱ በፊት ያለው እያንዳንዱ ሂደት ከከብት አያያዝ ጀምሮ እርድ እንዲሁም የቆዳ አቀማመጥ ላይ ከጥንቃቄ ጉድለት ብዙ ችግር ያጋጥማል ፡፡ በየጊዜው የሚደረገውም የዋጋ ጭማሪ ሌላ ፈተና ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከአቅራቢዎች ጋር በቅርበት ሆኖ ከመነጋገር ባለፈ ሌላ መፍትሄ የለም፡፡

ሌላው በዘርፉ የሚያጋጥመን ፈተና የሰለጠነ የሰው ሀይል አለማግኘት ነው፡፡ የምንሰራበት ዘርፍ ፋሽን መር በመሆኑ በየጊዜው የሚቀያየረውን ፋሽን ተከትሎ አብሮ ስራውን የሚያዳብር ሰራተኛ እምብዛም አይገኝም፡፡ ለዚህ ደግሞ ድርጅታችን ምንጊዜም ቀጣይነት ያለውን ትምህርት እና ስልጠና እየሠጠን እንገኛለን፡፡

በስራ ፈጣሪነት አለም ውጣ ውረዶች በዝተው ተስፋ አስቆራጭ ነገር ቢያጋጥም እንኳን ዋናው ነገር አላማን ማሰብ እና ተስፋ አለመቁረጥ ተገቢ ነው፡፡ አሁን ትልቅ እክል የሆነብን የቅርብ ጊዜ ችግር የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እጅግ አስደንጋጭ ነገር ግን በአላማችን ፀንተን እንድንቆም ያደረገን አጋጣሚ ነው፡፡ … ኮሮና እኮ በጣም አስደንጋጭ ነበር፡፡ አብዛኞቹ መዳረሻዎቻችን ሎክዳውን ላይ ሲሆኑ ኤክስፖርት ቆመ፤ 80 በመቶ የሚሆኑ የታዘዙ ምርቶቻችን ተሰረዙ፡፡ በጣም ግራ የሚያጋባ ነገር ነበር” አስቀድመው የሰራተኞቻቸውን ደህንነት ጥበቃ እርምጃ የወሰዱት እነ ዳንኤል ለተወሰኑ ቀናት ቤታቸው እንዲቀመጡ ማድረጉን ይናገራል፡፡

“ልጆቹን ለ20 ቀን ቤት እንዲቀመጡ ካደረግን በኋላ እንዴት ይህንን ችግር መወጣት እንደምንችል፣በምን መልኩ ማለፍ እንደምንችል እና ማን ሊረዳን ይችላል የሚለውን ማሰብ ጀመርን፡፡ በዚያን ጊዜ እንዲረዱን ካናገርናቸው ተቋማት መሃል የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን አንዱ ነበር፡፡ ወዲያው ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር አገናኙን፡፡ የማስተር ካርድን ፋውንዴሽን ድጋፍ በቃ! ነፍስ አድን ነበር፡፡ በመጀመሪያ 12 ሰራተኞቻችንን ለመቀነስ ተገድደን የነበረ ቢሆንም በተደረገልን ድጋፍ ሌሎች ሰራተኞችን ጨምረን ለወቅቱ የሚያስፈልገውን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እያመረትን እንገኛለን፡፡

በአላማችን ፀንተን በመቆየት ተረጋግተን የመፍትሄ ሃሳብ ለማምጣት በመንቀሳቀሳችን ይሄን ድጋፍ በማግኘታችን ከመውደቅ ድነናል፡፡ እና አኔ በዛ ተስፋ አስቆራጭ ወቅት ድሮ አብሪያቸው እየሰራሁ ያሳደጉኝ ሰፈር ውስጥ ያሉ ትናንሽ ንግዶች ጋር በመሄድ እነሱ እንዴት ሊቋቋሙት እንደቻሉ አዋራቸው ነበር፡፡ ያ ትልቅ የመንፈስ ጥንካሬ ይሰጠኝ ነበር፡፡”
እንደነዚህ አይነት መካሪዎች በዙሪያው ስለመኖራቸው አመስጋኝ እንደሆነ የሚገልፀው ዳንኤል በስራ ያሳደጉት ሰዎች ባለውለታዎቹ እንደሆኑ ይናገራል፡፡

በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የአለም ክፍሎች ሱቆቻቸውን በድጋሜ እየከፈቱ መሆኑ ጎን ለጎን ወደ ዋናው ስራችን ለመመለስ አሁን መልካም ጊዜ ነው፡፡ ህይወት ከኮሮና ጋር እንኳን ቢቀጥል የቀድሞ ስራችንን እና ህይወታችንን ለማስቀጠል ዝግጁ ሆነን በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን፡፡በተጨማሪም ጊዜውን አዳዲስ ምርት ዲዛይን ለማፍለቅ እየተጠቀምንበት ነው፡፡

ብዙ ጊዜ የተለመደው የአፍሪካ ሀገራት ጥሬ እቃ ወደ ውጭ ገበያ ልከው የውጭ አገራት ደግሞ ያለቀለት ምርት መላክ ነው፡፡ እና ደግሞ ኢትዮጳያን በአለቀለት የቆዳ ምርት ለማስተዋወቅ ቀድመን የያዝነውን አላማ በማፅናት መዳረሻዎቻችንም ለማስፋት ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡ አሁን ያሉን ዋና ዋና መዳረሻዎች ጃፓን፣ አውሮፓ እንዲሁም አሜሪካ ናቸው፡፡” ኮት ኬት በተጨማሪም ወደ ሀገር ውስጥ ገበያ ለመግባት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ዳንኤል ገልጿል፡፡

ማህበራዊ ድህረ ገፅ ላይ ያጋሩ