“ለጀማሪ ስራ ፈጣሪነት የአዕምሮ ዝግጁነት ያስፈልጋል !”

የምትወደውን የአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ስራ ለ8 አመታት በአሜሪካን ሀገር ብትሰራም ፍላጎቷ ግን ገንዘብ እና ንብረት ከማፍራት ባለፈ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል ትርጉም ያለው ህይወት እንዲኖራት ነበር፡፡

“የሆነ ቀን ጠዋት እንደተለመደው ወደ ስራ እየሄድኩኝ የትራፊክ መብራት ጋር ቆሜ ይሄ አይነት ኑሮ እስከመቼ ነው የሚቀጥለው? ብዬ አሰብኩኝ፡፡ሁላችንም ብንሆን በህይወት ስንኖር የሆነ ጊዜ ላይ ትርጉም እንፈልጋለን፡፡የተለመደው ነገር ቤት፣ ገንዘብ እና ስራ ሲኖር ደስተኛ መሆን ነበር፡፡እኔ ግን እነዚህን አግኝቼ የሆነ ነገር እንደጎደለኝ ይሰማኝ ነበር፡፡

በ2012 ወደ አገሬ ተመልሼ የራሴን ስራ እየሰራሁ ለሌሎችም ስራ መፍጠር አለብኝ ብዬ የወሰንኩት ያን ቀን ነበር’’ ትላለች የጋበር ቴክስታይል ኃ.የተ.የግ.ማ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ ጃኔት፡፡

“ ትውልዴና እድገቴ አዲስ አበባ ነው፡፡አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተማርኩት ሊሴ ገ/ማርያም ትምህርት ቤት ውስጥ ሲሆን የደረጃ ተማሪ ነበርኩ፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ጎን ለጎን ለፋሽን ዲዛይን ዝንባሌ ስራ ነበረኝ የፋሽኑ ዓለም ምን ላይ እንዳለ አዘውትሬ እከታተል ነበር፡፡ በትምህርቴ ወደ ሳይንሱ እና ወደ ሂሳቡ አድልቼ የፋሽኑን ነገር በልጅነቴ ባላዳብረውም ግን ሁሌም ውስጤ ያለ ነገር ነበር፡፡ በዛ ላይ መቼ እና እንዴት የሚለውን ነው እንጂ ያላስቀመጥኩት የሆነ ጊዜ ላይ ስራ ፈጣሪ እንደምሆን አውቀው ነበር፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ከጨረሰኩ በኋላ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ሄድኩ፡፡ ከጆርጂያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዬን በአካውንቲንግ አግኝቻለሁ፡፡በመቀጠልም ለ8 አመታት ያህል በአካውንቲንግ ፋይናንስ እና የውስጥ ኦዲት ስራ ስሰራ ቆይቻለሁ፡፡

ሁለቱም ወላጆቼ የራሳቸውን ስራ የሚሰሩ መሆናቸው እኔም ፈለጋቸውን እንድከተል አድርጎኛል፡፡ ሞራል ሆኖ ያነሳሳኝም ይኸው ነበር፡፡ ከምንም በላይ ግን ለውጥ የሚያመጣ የስራ ዕድል በማመቻቸት በጎ ተፅዕኖን ማሳደር የምንጊዜም ፍላጎቴ ነበር፡፡

ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል ህይወት እንዲኖረኝ ነው! ለፋሽን ዲዛይን ፍላጎት ስላለኝ ይሄን ዘርፍ መምረጤ ደግሞ እንዳሁኑ የጨርቃጨርቁ ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ ስለመጣና በይበልጥ ሴቶችን ስለሚያሳትፍ ነው፡፡ ትላለች፡፡”

ጃኔት ስለ ትምህርትና የስራ አጀማመር ጊዜዋ ስታስታውስ በ2016 እኤአ ነበር ጋበር ቴክስታይል ኃ/የተ/የግ/ማ የተመሰረተው፡፡ በጋበር ቴክስታይል ድርጅት ስር ለተለያዩ ድርጅቶች ልየ ልዩ ዓላማ የሚውሉ የቲሸርት እና ሹራብ ስራዎች፣የደምብ ልብሶች እንዲሁም ዕለት ተዕለት የሚለበሱ ከ18 ዓመት እስከ 39 ዓመት ላሉ ወጣቶች የሚሆኑ ልብሶች የሚመረቱበት 3 ክፍሎች አሉት፡፡

አብዛኛው ገበያው በአገር ውስጥ ቢሆንም በተለያዩ አለም አቀፍ ባዛሮች እንሳተፍ ነበር ፡፡ ወደፊትም ምርታችንን ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ ዕቅድ አለን፡፡

ድርጅቴን የከፈትኩት በግሌ በቆጠብኩት እና ቤተሰቦቼ በገዙት አክሲዮን በጥቅሉ በ5 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ነበር፡ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ ድርጅቴን ለመክፈት መንቀሳቀስ ስጀምር በጣም የፈተነኝ ነገር ካለው የአሰራር ስርዓት ጋር መግባባት አለመቻሌ ነበር፡፡ እኔ በ18 አመቴ ከአገር ስለወጣሁ አሜሪካን ሀገር ያለውን ፈጣን አሰራር ነው የማውቀው፡፡ እዚህ ስመጣ መስሪያ ቤት ገብቼ ወዲያው ጉዳዬን ጨርሼ የምወጣ መስሎኝ ነበር፡፡

ከዚህም ባለፈ ሸማቾች ለአገር ውስጥ ምርቶች ያላቸው አቀባበል ዝቅተኛነት ሌላው ነበር፡፡ ይህ አመለካከት ግን መቀየር አለበት የሚል አስተሳሰብ አለኝ ፡፡እርግጥ በተለያዩ ተቋማት የአገር ውስጥ አምራቾችን ለማስተዋወቅ በሚሰራው ስራ መጠነኛ ለውጥ እየተስተዋለ ቢመጣም የአገር ውስጥ ምርት ሲባል ርካሽ እና ጥራት የሌለው ነው የሚለው በገዢዎች ዘንድ ያለ አስተሳሰብ እጅግ ተስፋ አስቆራጭ ነበር፡፡

ይሄ አይነቱ የሰዎች ምላሽ በተለይ መጀመሪያ አካባቢ ተስፋ ያስቆርጠኝ ነበር፡፡እየቆየሁ ግን ስለ ስኬታማ ስራ ፈጣሪዎች የተፃፉ ፅሁፎችን ሳነብብ የዚያ አይነቱ ስሜት የሚያጋጥም እና የተለመደ መሆኑን ከምንም በላይ ደግሞ ስኬት በአንድ ጀምበር እንደማይመጣ ተረዳሁ፡፡ አሁን ግን ጠንካራ ሆኛለሁ፡፡ እንዲህ አይነት ነገር ቢያጋጥመኝ እንኳን የማተኩረው ወደ መፍትሄ መፈለጉ ላይ ነው፡፡

በተጨማሪም የሰለጠነ የሰው ኃይል ማግኘት እጅግ ከባድ ነገር ነው፡፡ በእኔ ድርጅት የሚሰሩ ሰራተኞች ከስር ጀምሮ ተከታታይ ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ እንዲያድጉም እናደርጋለን፡፡

በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ 75 ሰራተኞች አሉን፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 90 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡ ቀድሞም ቢሆን ለፋሽን ካላኝ ፍላጎት ጎን ለጎን በተለይ ለሴቶች የስራ ዕድልን ለመፍጠር እመኝ ነበር፡፡ ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ስራ ለማግኘት ሲቸገሩ አስተውላለሁ፡፡ እኔ ደግሞ የምፈልገው በገንዘብ እራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ነው፡፡
እንዲያም ሆኖ ግን በስራ ፈጣሪ አለም አንዱ ሲሞላ ሌላው መጉደሉ የተለመደ ነውና ሰሞነኛው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስራችንን በእጅጉ ፈትኖታል፡፡

ምንም እንኳን ሰራተኛ ቅነሳ በቀጥታ ባላደረግም መንግስት ባወጣው የተሸከርካሪዎች ጎዳና ላይ መውጫ መመርያ መሰረት ለድርጅቱ ሰራተኞች እንደልብ የሰርቪስ አገልግሎት መስጠት አልቻልኩም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ጥቂት የማይባሉ ሰራተኞች በስራ ገበታቸው ላይ ላለመገኘት ተገድደዋል፡፡

ለሰራተኞች ሰርቪስ እንደልብ ማቅረብ መቸገራችን ብቻም ሳይሆን ሁሉም ምርት እና ገበያ የተቋረጠብን ሙሉ በሙሉ ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት ለሰራተኛ ደሞዝ ለመክፈል እንኳን እንዲያስችለን ብለን ለጊዜው በጣም አስፈላጊ የሆኑትን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማምረት ጀመርን፡፡ እሱንም ቢሆን ለማምረት የሚረዳን ጥሬ እቃ መግዣ ገንዘብ እጥረት ነበረብን፡፡ ድርጅቱን ለመዝጋትም ተቃርበን ነበር፡፡ እንዲህ በተቸገርንበት ወቅት ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ዘርፍ ላይ ያሉና ሁኔታውን ለመቋቋም ጭምብል ማምረት ከጀመሩ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን የማስተርካርድ ፋውንዴሽንን ድጋፍ ጠየቅን፡፡ይሄ ድጋፍ ያሉንን ሰራተኞች ከመፈናቀል ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ሰራተኛ እና ማምረቻ ማሽኖች እንዲኖረን ረድቶናል፡፡ ነገሮች እንዲህ ሆነው ቢቆዩም እንኳን ለተከሰተው ወረርሽኝ ከድርጅታችን የሚጠበቅብንን ድርሻ መውጣታችን እንዳለ ሆኖ ወደ ቀድሞ ገበያችን ለመመለስ የምንችልበትን እቅድ በማውጣት ወደ ስራ ለመግባት በዝግጅት ላይ ነን፡፡

የነበሩን ደምበኞች ጋር ግንኙነታችንን ለማስቀጠል ከመሞከር በተጨማሪ ወደ ገበያው ለመመለስ አዳዲስ ገዢዎችንም መፈለግ ይኖርብናል፡፡ ገበያው ሙሉ ለሙሉ ቆሞ ስለነበር እንደአዲስ የሚሰሩ ብዙ ነገሮች ይኖራሉና እነሱን ጎን ለጎን አጠናክረን እየሰራን ነው፡፡ከዚህ የስራ ፈጣሪነት ጉዞ በጣም ፈታኝ እንደሆነ አይቼዋለሁ፡፡ ቀላል መንገድ አይደለም! በተለይ ለጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች ማለት የምፈልገው ነገር የአዕምሮ ዝግጁነት ያስፈልጋል ነው፡፡ ምክንያቱም ጀማሪ ስራ ፈጣሪ ሲኮን የሚፈለገው ነገር ሁሉ ተሟልቶ አይኖርም፡፡ ብዙ የሚገድቡ ነገሮች ይኖራሉ፡፡ የቢዝነሱ ፈጣሪም፣ ሽያጭ ባለሞያም ፣ የፋይናንስ ባለሞያም መሆን ሊያስፈልግ ይችላል የስራ ፈጣሪነት መንገድ ቀላል እንዳልሆነ እና የአዕምሮ ዝግጁነት እንደሚያስፈልግ መታወቅ አለበት፡፡ማንም ሰው በፈጠራ ችሎታው ወይም ልዩ በመሆኑ ማፈርም ሆነ ከመስራት ወደ ኋላ መቅረት የለበትም፡፡’’ ትላለች ጃኔት፡፡

ማህበራዊ ድህረ ገፅ ላይ ያጋሩ