የኢፌዲሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን እና የዘርፉ ሥራ ዕድል ፈጠራ ባለድርሻዎች በተገኙበት የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ር/ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸው በተለያዩ ግጭቶች ከ 18ሺህ በላይ ኢንተርፕራይዞች በመውደማቸው በዚህ ዓምት የምንሰራው የሥራ ፈጠራ ሥራ ከሌላው ጊዜ ይለያል ብለዋል፡፡

የኢፌዲሪ ሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላችው ባለፈው ዓመት የታቀደውን ሦስት ሚሊዮን የሥራ ዕድል የመፍጠር ዕቅድ ማሳካት መቻሉን ገልፀዋል፡፡ ይህ ዓመታዊ መድረክ ድክመቶቻቸንን የምናርምበት ነው በማለትም ቀጣዩ ሥራ ከዓመታዊ ዕቅዳችን ለሦስት ሚሊዮን ዜጎች ሥራ ዕድል ከማመቻቸት ባሻገር በጦርነት እና በግጭት ምክንያት የወደሙ ኢንተርፕራይዞችን ከመደገፍ አኳያ እና ከመካከለኛው ምስራቅ ከ43ሺህ በላይ ዜጎች የተመለሱበት በመሆኑ ዕቅዳችንን በመከለስ ደግመን ለማቀድ የተገደድንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራ አካላት የሆኑት ከፌደራል ተቋማትና ከክልሎች እንዲሁም ከፋይናንስ ተቋማት ተወክለው የተገኙ እንግዶች የተገኙበት የሁለት ቀኑ ግምገማ በክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በ2013 ዓ.ም የተሰሩ ሥራዎች አፈጻጸም፤ የታዩ ክፍተቶች ፤ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና በመፍትሔ አቅጣጫዎች ዙርያ በመወያየት የ2014 በጀት ዓመት ዋና ዋና የትኩረት ነጥቦች ላይ ምክክር ተደርጎ የክልሎች የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርትም በዚሁ መድረክ ቀርቧል፡፡

በዓመታዊ መድረኩ የኮቪድ19 ወረርሽኝ ተፅዕኖ ጥናት ግምገማ የሚቀርብበት ሲሆን በሥራ ገበያው ውስጥ ሁሉንም ዜጎችን ማካተትን በተመለከተ ኮሚሽኑ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያካሄደው ጥናትም ውይይት ይደረግበታል፡፡
የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በየዓመቱ ሦስት ሚሊዮን የሥራ ዕድሎችን በተለይም በግብርና፣ በኢንዱስትሪ ፣ በአገልግሎት እና ሌሎችም ዘርፎች በመፍጠር እስክ 2022 ዓ.ም ይህንን ቁጥር 20 ሚሊዮን ለማድረስ እየሰራ ይገኛል፡፡

ያጋሩት