“እናት ሥራ መሥራት ቢኖርባትም ከልጆቿ መራቅ ግን የለባትም!”
በወጣትነት ዕድሜዋ የሶስት ልጆች እናትና ስኬታማ ሥራ ፈጣሪ መሆን በመቻሏ በዙሪያዋ ያሉ ሰዎች እንደሚገረሙ የምትናገረው ፍቅርተ “የሠራተኛ እናት ዋናው ትግል በኢኮኖሚ ከማደግ ባለፈ ለልጆቿስ ምን ያህል ጊዜ መስጠት ትችላለች የሚለው ነው” ትላለች፡፡
“ሴቶች ካሉባቸው ተደራራቢ የቤተሰብ ኃላፊነቶች መካከል ልጅ ማሳደግ አንዱ ነው። ለበርካታ ሴቶች ወደ ሥራ ቦታ ልጆቻቸውን ይዘው መምጣት የማይመች ሁኔታ አለው። ቤት ትተው ለመምጣትም ቀላል አይሆንም። ሴቶችን ባሉበት በሚመቻቸው ቦታ ሆነው እንዲሰሩ አቅማቸውን ማጎልበት የተሻለ ነው። እነ ራሴ የ ሦስት ልጆች እናት ነኝ። የራሴን ሥራ ለመሥራት የወሰንኩት ለዲዛይን ካለኝ ፍቅር ባሻገር ለልጆቼ የእናትነት ጊዜየን እንደፍላጎቴ መስጠት እንዲያስችለኝ ነው” ትላለች የግል ሥራ ለመሥራት የወሰነችበትን ምክንያት ስታስረዳ።
በድርጅቷ ውስጥ የሚሰሩ እናቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ በጣም ይበረታታሉ። በተለይም ሥራቸውን ልጆቻቸው አጠገብ ሆነው መሥራት እንዲችሉ ማቅረብ የምትችለውን ሁሉ እንደምታቀርብላቸው ዲዛይነር ፍቅርተ ትናገራለች፡፡
“ፍቅርተ እና ቤተሰቦቿ ዲዛይን ኃ.የተ.የግ.ማ የተመሰረተው በ2009 ዓ.ም ነው። ወደ እዚህ ሥራ ከመግባቴ በፊት ተምሬ እሠራ የነበረው በዴቨሎፕመንታል ሳይኮሎጂ የሥራ መስከ ሲሆን በዘርፉ የመጀመርያ እና ሁለተኛ ዲግሪየን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቀብያለሁ፡፡ ምንም እንኳን ከልጅነቴ ጀምሮ “እሷን ተዋት መቆራረጥ ትወዳለች!” እስክባል ድረስ የዲዛይን እና የስፌት ፍቅሩ ቢኖራኝም በስነ-ልቦና ትምህርት እስከመጨረሻው በመዝለቅ አስተማሪ ለመሆን አቅጄ ነበር ፡፡
ይሁን እንጂ ካቀድኩት ይልቅ የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ጀምሮ በእናቴ የስፌት ማሸን የራሴን ዲዛይን በመሥራት በትምህርት ቤታችን ውስጥ ይዘጋጁ በነበሩ የፋሽን መድረኮች ላይ ስሳተፍበት የነበረው የልጅነት ፍላጎቴ አሸንፎ ዛሬ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ዘመነኛ የባህል ልብሶች ዲዛይነር እና አምራች ለመሆን በቅቻለሁ፡፡
ከቀድሞ ሥራዬ ያተረፍኩት ገንዘብ ስላልነበረኝ ሥራውን ለመጀመር ሳስብ ባለቤቴ በሰጠኝ 20 ሺህ ብር የመሥሪያ ቦታ ተከራየሁ። ለስነ-ልቦናው ትምህርት ፍቅሩ ስለነበረኝ የራሴን ሥራ በጀመርኩባቸው ወራት ጊዜ እያመቻቸሁ እሠራው ነበር። ንግድ ፍቃድ አውጥቼ፣ ሥራዬ ብዬ ባላተኩርበትም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለሁ የዲዛይን ሥራዎቼን በትውውቅ ለአንዳንድ ሰዎች እሠራ ስለነበር ድርጅቴን በከፈትኩበት ወቅት ቀድሞ የገነባሁት ትውውቅ ገበያ ለማግኘት አግዞኛል።
ድርጅቴን ስከፍት ምንም ሠራተኛ አልነበረኝም። ቀስ እያልኩ በአዲስ አበባና ጨንቻ አካባቢ ከሚገኙ የሽመና ሠራተኞች እና የህብረት ሥራ ማህበራት ጋር በጋራ መሥራት ጀመርኩ፡፡
አሁን 40 ሠራተኞች አሉኝ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 95% የሚሆኑት እናቶች ናቸው፡፡ እኔ ልጆቼን ለመቅረብ እና ጊዜ ለመስጠት ስል ነውና ይሄንን ሥራ የጀመርኩት እናቶችን ከቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ አደርጋለሁ።
በርካታ ሴቶች ልጅ ሲወልዱ ከሥራ ይቀራሉ። ኑሮ ደግሞ በአንድ ሰው ገቢ ብቻበቂ ስለማይሆን በኢኮኖሚ ቤተሰባቸውን ለመደገፍ ወጥተው ይሠራሉ። ልጆች በዚህ ወቅት እንክብካቤ ይጎድልባቸዋል። አለፍ ሲልም ጉዳት ይደርስባቸዋል። ይሄ ደግሞ ለእናቶች በጣም ከባድ ነገር ነው፡፡ ለልጆቻቸው ሲሉም ሳይሰሩ ቤት እንዲቀመጡ የሚያደርጋቸው ይህ ነገር ነው፡፡ ሊያጋጥሙ ከሚችሉ ሌሎች ችግሮችም በተጨማሪ ህጻናቱን ጡት ለማጥባት እና እናት አጠገባቸው መሆኗ ግድ ነው፡፡
ይሄንን ለስነ-ልቦናው ቅርብ በመሆኔ እንዲሁም በዘርፉ ላይ ስሠራም የእናቶችን ጉዳይ በቅርበት ስለማውቀው በቀላሉ እረዳለሁ፡፡ ስለዚህ ልጆቻቸውን አጠገባቸው ሆነው እንዲያሳድጉ እና የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመቀነስ ስል እኔ ወደ እነሱ እሄዳለሁ እንጂ እነሱ ወደ እኔ አይመጡም፡፡
የሹራብ ሥራ የሚሠሩት ሴቶች ዲዛይኑ ከወጣላቸው በኋላ በየቤታቸው ሠርተው የሚያስረክቡ ሲሆን የስፌት ሥራ ለሚሰሩት ደግሞ ቤት ሆነው የሚሰሩበት ማሽን ተሰጥቷቸዋል። ብዙ ሰዎች “ሳትቆጣጠሪያቸው ውጪ ሆነው ሲሰሩ እንዴት ታምኛቸዋለሽ?” ይሉኛል፡፡ በምርት ሥራ ዋናው ነገር ሥራው የትም ይሰራ የትም በጥራትና በጊዜው መሰራትና መድረሱ ነው። ሠራተኞቼ የሚከፈላቸው ደግሞ ሠርተው ባደረሱት ልክ ነው። ለኔ ዋጋ ያለው ቦታው ሳይሆን ውጤቱ ነው። እንዲያውም በጊዜው በሰዓት ገባችሁ አልገባችሁ ከሚል የቁጥጥር ሥራ ገላግሎኛል።
ወደ እዚህ ሥራ ስገባ በግሌ ዲዛይን ሰርቼ ልብስ ከመሸጥ በተጨማሪ በዙሪያዬ ላሉ ሰዎችም ራሳቸውን ችለው ማደግ የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸትም ዓላማዬ ነበር፡፡ ይህንን አሰራር እና የገበያ ሰንሰለት ለመፍጠር እንዲሁም ለማሰልጠን ረጅም ጊዜ ወስዶብኛል፡፡ ያልተለመደ ቢሆንም እኛ እየሰራንበት ነው፡፡ እርስ በእርሳችን ተያይዘን ለማደግ የምንረዳዳበት ቢዝነስ ነው፡፡ እኔ ጋር ተቀጥረው የነበሩ አሁን የራሳቸውን ፍቃድ አውጥተው እየሰሩ ያሉ እናቶች አሉ፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በፊት ሥራችን ጥሩ እየሄደ ነበር። የአገር ውስጥ ገበያው ወቅትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ትኩረቴ በይበልጥ በውጪው ገበያ ላይ ነበር። ካፒታሌንም ወደ 1.5 ሚሊየን ብር አሳድጌ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ አሳድሮብኛል፡፡
በባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ከፈረንሳይ ተቀብዬ የመጣሁትን ትልቅ ትዕዛዝ ጨምሮ ብዙ የውጭ ገበያ ምርቶች ተቋርጠውብኛል፡፡ በአገር ውስጥም ቢሆን ወቅትን ጠብቆ ይመጣ የነበረው የሰርግ ሥራ በኮቪድ -19 ስርጭት ምክንያት በርካታ መርሃ ግብሮች በመሰረዛቸው የሱቅ ኪራይ ወጪን እንኳን መሸፈን ባለመቻሌ በአዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ የሚገኘውን ሱቄን ለመዝጋት ተገድጃለሁ፡፡በጣም አስደንጋጭ ጊዜ ነበር፡፡ ከሚያሳድረው ኢኮኖሚያዊ ጫና በተጨማሪ የራሱ የሆነ የስነልቦና ተፅዕኖ ነበረው፡፡ በተለይ የፋሽኑ ኢንዱስትሪ እጅግ ሰፊ ሰንሰለት ያለው በመሆኑ በጣም የተጎዳ ይመስለኛል፤ እኛ እዚህ ቦታ ላይ ያለነው ለራሳችን መሆን እና በልተን ማደር ላይከብደን ይችላል፡፡ የጠላፊዎች እና የሽመና ሠራተኞች ሥራ ግን ሙሉ ለሙሉ ነው የተቋረጠው፡፡ ምን ያህል ሊከብድ እንደሚችል ማሰብ አያቅትም፡፡”
ከጊዜው ጋር ተስማምታ ሥራዋን ማስቀጠል እንዳለባት የገባት ፍቅርተ የወሰደችው ፈጣን እርምጃ ነበር፡፡ እሱም በጊዜው የሚያስፈልጉትን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን ባላት ገንዘብ ተጠቅማ መሥራት ነበር፡፡
“ያሉኝን ሠራተኞች ሳልቀንስ ተጨማሪ የሥራ ዕድል ፈጥሬ እና ማሽኖችን ጨምሬ የማስክ ሥራዬን እንዳጠናክር የደረሰልኝ በሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በኩል ያገኘሁት ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ድጋፍ ነበር፡፡ የኮሮና ቫይረስ ባይጠፋም እንኳን ሰው መልበሱን አያቆምም! የሥራ ፈጣሪነት ዋናው መለኪያ ከክስቶች ጋር ተላምዶ እና ፈተናዎችን ተጋፍጦ ማምለጫ መንገድ ማዘጋጀትና የሥራ ማስቀጠያ ዘዴን መፈለግ ነው፡፡ ለሀገር ውስጥ ገበያ የሰርግ ልብሶች አዋጪ አለመሆናቸውን ስለተረዳሁ ዕለት ተዕለት መለበስ የሚችሉና ዋጋቸው ተመጣጣኝ የሆኑ ዘመነኛ የባህል ልብሶችን ለማምረት ዕቅድ አለኝ ፡፡ የፋሽን መድረኮች መዘጋጀት ባይችሉ እንኳን ሰዎች ልብሶቻችንን ኢንትርኔት ላይ መግዛት ይችላሉ! አሁን እያመረትኩ ካለው የአፍና የአፍንጫ መሽፈኛ ጭምብል ሥራ በተጨማሪ የተቋቋምኩለትን ዓላማ እንዴት ጎን ለጎን ማስቀጠል እንዳለብኝ አቅጄ እየሰራሁ ነው፡”