ስድስት የመንግሥት ተቋማት የቅንጅት መድረኮች የተቋቋሙ ሲሆን እነዚህ መድረኮች እስከአሁን ቢያንስ አንድ ጊዜ ስብሰባቸውን አካሂደዋል፡፡ እነዚህ መድረኮች ተጠሪነታቸዉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚመራው የስራ እድል ፈጠራ እና ኢንቨስትመንት አብይ ኮሚቴ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ከሚሽነር ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ ቁልፍ ሚና ያላቸውን የ10 ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ኃላፊዎች/ሚኒስትሮች እና ሁሉም የክልል ፕሬዝዳንቶች የዚህ አብይ ኮሚቴ አባላት ናቸው፡፡ የኮሚቴ አባላቱ በስራ ዕድል ፈጠራ ረገድ የሚከናወኑ ተግባሮችን ለመከታተልና ለመገምገም በየሁለት ወሩ በመሰብሰብ ይመካከራሉ፡፡
በተጨማሪም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና በስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር በጋራ የሚመራ ብሔራዊ የስራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት የተመሠረተ ሲሆን ይህ ምክር ቤት ሁሉም ባለድርሻ የመንግሥት ተቋማት በስራ ዕድል ፈጠራ ረገድ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ስለመሆናቸው ይከታተላል፡፡
በስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር የሚመራ አብይ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ተመስርቷል፡፡ ይህ በስራ ዕድል ጉዳይ ቁልፍ ሚና ያላቸወን 10 ሚኒስትሮች ያካተተ ኮሚቴ በሁሉም ሴክተሮች ለጋራ እቅድ ዝግጅት፣ ሪፖርት እና ግምገማ በወር አንድ ጊዜ ይሰበሰባል፡፡ በዚህ አብይ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ሥር አግባብነት ባላቸው ሚኒስትሮች የሚመሩ ስድስት ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረዋል፡፡እነዚህም የባህሪ ለውጥ የክህሎት ማዳበሪያ እና አቅም ግንባታ ንዑስ ኮሚቴ፣ የከተማ ስራ ዕድል ፈጠራ ንዑስ ኮሚቴ፣ የገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ ንዑስ ኮሚቴ፣ የግል ዘርፍ ስራ ዕድል ፈጠራ ንዑስ ኮሚቴ፣ የመንግስት ዘርፍ ስራ ዕድል ፈጠራ ንዑስ ኮሚቴ እና የውጭ ስራ ቅጥር ንዑስ ኮሚቴ ናቸው፡፡ ከየሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና ከኮሚሸኑ የተውጣጡ ሙያተኞች የተካተቱበት የቴክኒክ ኮሚቴ አብይ የሚኒስትሮች ኮሚቴዉ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች ተግባራዊ ያደርጋል፡፡
ሌላው ተጠቃሽ የቅንጅት መድረክ ከስራ እና ቅጥር ጉዳዮች ጋር ቀጥተኛ ግኑኝነት ያላቸውን የፌደራልና የክልል መንግስታት ተቋማት፣ የፋይናንስ ቢሮ እና የፕላን ቢሮ ሃላፊዎችን ያካተተ በየሩብ ዓመቱ የሚሰበሰብ የፌደራልና ክልል የጋራ መድረክ ነው፡፡ ይህ መድረክ የተመሠረተበት ዋና ምክንያት በሀገር ደረጃ በሚወጡ የስራ ዕድል ፈጠራ ግቦች ዙሪያ ሁሉም የባለቤትነት መንፈስ እንዲኖረው፤ በስራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ ዝግጅት፣ አፈፃጸም ፣ ክትትልና አመራር ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖር ለማድረግ ነው፡፡
ይህ ፎረም የስራ ዕድል ፈጠራ ግቦችን ወደ ክልል ደረጃ የማውረድ እና ወጥነት ያለው አሰራር እንዲኖር የማድረግ፤ የትኩረት መስኮችን የመለየት ፤ የአቻ ግምገማ የማድረግ እንዲሁም በሁሉም የአስተዳደር እርከን ደረጃዎች በስራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ የተቀናጀ አመራር እንዲኖር የማድረግ ኃላፊነት አለበት፡፡