የመንግስት እና የግል ዘርፍ አባላትን ያካተተ ከፍተኛ የልኡካን ቡድን በአሜሪካ ካሊፎረኒያ ግዛት የቴክኖሎጂ ኩባኒያዎች መነሃሪያ በሆነችው ሲሊከን ቫሊ ሲያደርግ የነበረውን ጉበኝት አጠናቋል፡፡ የልኡካን ቡድኑ በጉበኝቱ ወቅት ኢትዮጵያ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካኝነት እያደረገችው ስላለው የሥራ ዕድል ፈጠራ እና ኢኮኖሚ ልማት እንቅስቃሴዎች ለኩባኒያዎቹ ሃላፊዎች ሰጥተዋል፡፡

የልኡካን ቡድኑ እንደ ጉግል፣ ማይክሮሶፍት፣ ሲስኮ፣ ኦራክል፣ ሰታንፎርድ ዩኒቨርሰቲ፣ ፕላግን ፕሌይ፣ ዋይ ኮምቢኔተር፣ ቪ ኤም ዌር እና ከመሳሰሉት በዓለም ታዋቂ ከሆኑ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ኩባኒያ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው በኢትዮጵያ ስላለው የዲጂታል ገቢያ አቅም መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የቡድኑ አባላት በተጨማሪም ከኩባኒያዎቹ ሃላፊዎች ጋር በነበራቸው ውይይት እና የኩባኒያዎቹን የሥራ እንቅስቃሴ በግንባር በመጎብኘት የዲጅታል ቴክኖሎጂ በአጠቃላይ ለኢኮኖሚ ልማት በተለይ ደግሞ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ሊኖረው ስለሚችሉው ሚና ሰፊ ግንዛቤ ለማግኘት ችለዋል፡፡

ኩባኒያዎቹ ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ የቴክኖሎጂ ዘርፎች አብሮ ለመስራት ባሳዩት ፍላጎትና በተደረሰው መግባባት መሠረት የቡድኑ አባላት ጉብኝት ውጤታማ እንደነበር መገንዘብ ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ጉግል ‘ጉግል ስነጥበብ እና ባህል’ (Google Arts and Culture) የተሰኘ ፕሮግራሙን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመተባበር ገቢራዊ በማድረግ ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ የባህልና ታሪካዊ ሃብት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማቅረብ ተስማምቷል፡፡ ይህም የቱሪዝምን ዘርፍ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡

የልኡካን ቡድኑ ታዋቂውን የጀማሪ ኢንተርፕራይዞች ደጋፍ ሰጪ ፕላግን ፕሌይ የጎበኙ ሲሆን ኩባኒያውም ኢትዮጵያ ውስጥ ጠንካራ የጀማሪ ኢንተርፕራይዞች ድጋፍ ስርዓተምህዳር እንዲኖር ዘመናዊ የድጋፍ መስጫ ማዕክል ለመመስረት ሃሳብ አቅርቧል፡፡

ቡድኑ በተጨማሪም ታዋቂውን የኔትዎርክ እቃዎች እና ሶፍትዌር አምራች ኩባኒያ ሲስኮን ጎብኝተዋል፡፡ በዚህም ወቅት የሲስኮ ኣካዳሚን ለማስፋፋት፣ ሲስኮ ኤጅ የተሰነዉን ፕሮግራም እና ዲጂታል የመማሪያ ክፍሎችን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማስጀመር፣ እንዲሁም የተፈናቃዮች እና ስደተኞች ዲጂታል አካታችነት መርሃግብር ለመተግበር ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

የቡድኑ የጉብኝት መርሃግብር ሌሎች ታዋቂ ኩባኒያዎችን እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ያካተተ ሲሆን ከነዚህ ኩባኒያዎች ጋርም ኢትዮጵያ ውስጥ የዳታ ማዕከሎችን መገንባት ስለሚቻልበት ሁኔታ፣ የኤሌክትሮኒክ የንግድ ልውውጥን ለማስፋፋት እንዲሁም ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር የኢንተርፕሩነርሽፕ ትምህርትን ማስፋፋት ስለሚቻልበት ሁኔታ ሰፊ ውይይት ተደርጎ ስምምነቶች ላይ ተደርሷል፡፡

ፎቶዎች ከጉብኝቱ


ያጋሩት