ጥቅምት 20 ቀን 2012፣ አዲስ አበባ—በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በቀጣዮቹ አመታት በሚተገበሩ ፖሊሲዎች፣ ፕሮግራሞችና አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ወደ 450 ቁልፍ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የመጀመሪያው ሀገር አቀፍ የሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ጉባኤ ዛሬ ተካሄደ፡፡

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ መስተዳድር፣ ሚኒስትሮች፣ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ ከነቲባዎች፣ አማባሳደሮች፣ የልማት አጋር ድርጅቶች ተወካዮች፣ የግሉ ዘርፍ ፣ የሴቶችና የወጣቶች ተወካዮች በጉባኤው ላይ ተሳትፈዋል፡፡

ክቡር አቶ ደመቀ ባደረጉት ንግግር በአሁኑ ጊዜ ኢትየጵያ ውስጥ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚሆን አዲስ ሥራ ፈላጊ ወጣት በየዓመቱ ወደ ሥራ ገበያው እንደሚቀላቀል አውስተዋል፡፡ አክለውም “ከአምስት አመት በኋላ ለ’አቅመ-ሥራ’ የሚደርሰው ኢትዮጵያዊ ቁጥር 94.2 ሚሊዮን የሚደርስ ሲሆን በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ አገሪቱም 14 ሚሊዮን ለሚሆኑ የሥራ ገቢያውን ለሚቀላቀሉ አዲስ ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል መፍጠር አለባት” ሲሉ አስገንዝባዋል፡፡

“እነዚህ የስነህዝብ አሃዞች አሁን ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ፤ ከፍታችን የተደቀነው ‘ሥራ የመፍጠር ሥራ’ም ምን ያህል አቀበት የበዛበት እንደሆነ አመላካች ናቸው” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ምንግስት ይህን ከባድ ፈተና ያለበትንም ኃላፊነት በሚገባ ስለሚገነዘብ የወቅቱ የሀገራችን ዋና የትኩረት አጀንዳ የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳይ የሆነው” ብለዋል፡፡

“የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ” እና የኢትዮጵያን ለሥራ ምቹነት ማሻሻያ ፕሮግራሞችን ጨምሮ መንግስት በቅርቡ ያስጀመራቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያና ሌሎች የሪፎርም መርሃግብሮች ዋና ማጠንጠኛም ይኸው የሥራ ዕድል ጉዳይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የፌደራል የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ኤፍሮም ተክሌ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ኮሚሽኑ ከተቋቋመ በኋላ በቁሳቁስና እና በሰው ኃይል የሚያስፈልጉትን መሰረታዊ ግብአቶች በፍጥነት በማሟላት ወደ ስራ መግባቱን አውስተዋል፡፡

ኮሚሽኑ ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ካከናወናቸዉ አበይት ተግባራት መሃክል የሀገሪቱን የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉዳዮችን የሚመሩና የሚያስተባብሩ መዋቅሮችን በየደረጃው የማደራጀት፣ የፌዴራልና የክልሎች የስራ ዕድል ፈጠራ የጋራ መድረክን የማዋቀር፣ በሁሉም ክልሎች ከወረዳ እስከ ክልል አመራሮች የተሳተፉባቸው የአመራር ንቅናቄዎችን የማኪያሄድ ሥራዎች እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡

በጉባኤው ወቅት ተሰብሳቢዎች ከተወያዩባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መሃክል ይፋ የተደረገው “የስራ ዕድል ፈጠራ የተግባር መርሃግብር” አንዱ ነው፡፡ ይህ ዕቅድ በአገሪቱ ምቹ የሥራ ከባቢ እንዲኖር በማድረግ አዲስ ሥራ ፈላጊዎችንና ነባር ስራ አጦችን ወደስራ በማስገባት እስከ 2017 ዓ.ም 14 ሚሊዮን የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመ አገራዊ ዕቅድ ነው፡፡ የስራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ የተዘጋጀው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የግሉ ዘርፍና የመንግሥት በለድርሻ አካላት ጋር ጥልቅና ሰፊ ውይይት በማድረግ ነው፡፡

ሌላው በጉባኤው ላይ ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያን የሥራና የቅጥር ወቅታዊ አቋም የሚተነትነው “የሥራ ሁኔታ ሪፖርት” (‘The State of Jobs’ report) ነው፡፡ ይህ የመጀመሪያው የሆነው አመታዊ ሪፖርት ስለ ሀገሪቱ የስራ ዕድል ሁኔታ ጥልቅ ፍተሻና ትንተና ያካተተ ሲሆን በተጨማሪም የኢትዮጵያ ህዝብ ኑሮውን ለማቃናት ያለውን የስራ ዕድልና ተስፋ ያመላክታል፡፡

የፌደራል የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በቅርቡ የተመሰረተ የሀገሪቱን የቅጥርና የስራ ዕድል ፈጠራ አጀንዳ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁም ከዛ በታች ባሉ የመንግስት መዋቅሮች ለመምራትና ለለማስተባበር ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖ የተዋቀረ አዲስ የመንግስት ተቋም ነው፡፡ኮሚሽኑ በተጨማሪም አዳዲስ የስራ አማራጮችን በመለየት ያሰናዳል፣ በአገሪቱ ውስጥ ለሚከናወኑ የስራ ዕድል ፈጠራ ተግባሮች ማሳለጫ መድረኮችን ያመቻቻል፣ ሴክተር ተኮር የስራ ዕድል ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀት ያከናውናል፣ ለስራ እድል፣ ለግሉ ዘርፍ ዕድገትና በሥራ ገበያው ውስጥ የሚስተዋለውን የክህሎት ክፍተት ለማሟላት የሚያግዙ ፖሊሲዎችን ያዘጋጃል፣ ያስፈጽማል ፡፡

ፎቶዎች ከጉባኤው


ያጋሩት